የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ 'ጉብኝቴ ቻይና ለኢትዮጵያ መንግሥት ያላትን ድጋፍ ያሳያል' አሉ

የቻይና እና የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች

የፎቶው ባለመብት, @mfaethiopia

የምስሉ መግለጫ, የቻይና እና የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸው ቻይና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያላትን ድጋፍ ያሳያል ስለማለታቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።

ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 22/2014 ዓ.ም ንጋት ላይ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝነት አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩም ሆነ አዲስ አበባ የመጡበት ምክንያት እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

ለቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀባበል ለማድረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ነበር።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ ዋንግ ዪ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ያላትን መተማመን እንደሚያሳይ እና ቻይና ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያላትን ድጋፍ የሚገልጽ ነው ስለማለታቸው የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ገልጿል።

የሁለቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች

የፎቶው ባለመብት, @mfaethiopia

የምስሉ መግለጫ, የሁለቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች

"ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግሮቻቸውን መፍታት ስለሚችሉ ቻይና በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ ገብነትን ትቃወማለች" ስለማለታቸውም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስፍሯል።

ቻይና በቅርብ ወራት በተለይ ደግሞ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ መድረኮች ላይ ድጋፏን ስትገልጽ ቆይታለች።

የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው ቻይና፤ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ መክሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዳያወጣ ሲቃወሙ ከነበሩ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ከዚህ ቀደም ቻይና፣ ሕንድ እና ኬንያ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው፤ የፀጥታው ምክር ቤት ሊያወጣ የሚችለው የውሳኔ ሐሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና አንድነት ሊጻረር የሚችል ነው በማለት ተቃውመውታል።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በሁለቱ አገራት ወዳጅነት ያልተቀየረውን የቻይናን አቋም አድንቀዋል ተብሏል።