የደብረ ብርሃን መታወቂያ የሌላቸው ግለሰቦች በከተማዋ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተገለጸ

በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን የከተማዋ መታወቂያ የሌላቸው ግለሰቦች ከህዳር 16/2014 ዓ.ም ጀምሮ በቀን እንቅስቃሴ ከማድረግ መታገዳቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የከተማዋ ነዋሪዎችና የደብረ ብርሃን ከተማ መታወቂያ ያላቸው ግለሰቦች ብቻ በቀን እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላሉ ብሏል።

ለዚህም የከተማው አስተዳደር የሰጠው ምክንያት "በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች ሰርጎ ገቦች በመግባት አካባቢን የማጥናትና መረጃ የመስጠት ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ስለተደረሰበት ነው" ብሏል።

"ሰርጎ ገቦችን መለየትና አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ነጻ ለማድረግ፣ ለከተማውና ለነዋሪዎች ደኅንነት ሲባል በከተማው በየትኛውም አካባቢ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪና መታወቂያ ካላቸው ሰዎች ውጪ በቀን እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም" ብሏል።

በጦርነቱ ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ የተጠለሉ ነዋሪዎችም በተዘጋጀላቸው መጠለያ እንዲገቡም ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

የትግራይ ኃይሎች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ሸዋ ሮቢት ከተማን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል። ይህንን በተመለከተ ምንም ገለልተኛ ማረጋገጫ የለም።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጦርነቱን ለመምራት ከወሰኑ በኋላ ጦሩ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገቡን እና ድሉም "በጣም ቅርብ" ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማፂያኑን ለመዋጋት ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን እመራለሁ ያሉ ሲሆን የትግራይ ተዋጊዎችም ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እያመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልል የተዛመተው ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስከተሉን ቀጥሏል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታትና የእርዳታ ድርጅቶች አመልክተዋል።