አፕል የእስራኤሉን የቴክኖሎጂ ድርጅት 'ደንበኞቼን ሰልሏል' ሲል ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፕል የተሰኘው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኤንኤስኦ የተባለው የእስራኤል ኩባንያ የአይፎን ተጠቃሚዎችን መረጃ ለመመዝበር [ሃክ] ሞክሯል በሚል ከሰሰ።
ኤንኤስኦ የሚያመርተው ፔጋሰስ የተሰኘው ሶፍትዌር አይፎንና አንድሮይድ ስልኮችን የሚያጠቃ ሲሆን የአጭር የፅሑፍ መልዕቶችን፣ ፎቶዎችና ኢሜይሎን ለመመዝበር እንዲሁም የስልክ ንግግሮችን ለመጥለፍ የተዘጋጀ ነው።
ኤንኤስኦ ግሩፕ "እኔ ዒላማ ያደረግኩት አሸባሪዎችንና ወንጀለኞችን ነው" ይላል።
ነገር ግን ይህ ሶፍትዌር የመብት ተሟጋቾችን፣ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ለመጥለፍ ጥቅም ላይ ውሏል የሚል ክስ ይቀርብበታል።
ድርጅቱ፤ ፔጋሰስ የተሰኘው ሶፍትዌር የማቀርበው በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥሩ ታሪክ ላላቸው አገራት የጦር አባላትና ለሕግ አስከባሪዎች ነው ይላል።
ነገር ግን በያዝነው ወር መባቻ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሶፍትዌሩ "ሌሎች አገራት ሌላ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦችን፣ ጋዜጠኞችንና አክቲቪስቶችን" ለመሰለል እንዲችሉ አድርጓል በሚል በጥቁር መዝገብ ላይ እንዲሰፍር አድርገዋል።
አፕል ኩባንያውን የከሰሰው እንደ ማይክሮሶፍት፣ ሜታ፣ አልፋቤት ያሉ ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎች ቅሬታቸውን ካሰሙ በኋላ ነው።
አፕል በለቀቀው መግለጫ ኤንኤስኦ ግሩፕና እህት ኩባንያው ኦኤስዋይ ቴክኖሎጂስ "የአፕል ተጠቃሚዎችን ዒላማ በማድርጋቸው ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል" ብሏል።
ወደፊት ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ኤንኤስኦ የተባለው ኩባንያ ማንኛውንም የአፕል ምርት እንዳይጠቀም ይታገድ ይላል የአፕል ክስ።
ክሱን ዋሽንግተን ለሚገኝ ፍርድ ቤት ያቀረበው አፕል ኤንኤስኦ "የአሜሪካዊያን ዜጎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ስፓይዌር በመትከል ሰልሏል" ብሏል።
ግዙፉ አፕል ምንም እንኳ ይህ የእስራኤል ድርጅት ደንበኞቼን ሰለለ ቢልም የአፕል ‘ሰርቨር’ [ማዕከላዊ መረጃ ቋት] እንዳልተነካ ግን አስታውቋል።
ለክሱ ምላሽ የሰጠው ኤንኤስኦ "ምስጋን ለኛ ይሁንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ድነዋል" ብሏል።
"ሕፃናትን የሚበዘብዙና የሽብር ድርጊት የሚፈፅሙ ሰዎችን መንግሥታት እንዲቆጣጠሩ እኛ አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ እርዳታ እናደርጋለን" ይላል የድርጅቱ ምላሽ።












