የሎተሪ ገንዘብ ካልተሰጠን ያሉ የሜክሲኮ ታጣቂዎች መነጋገሪያ ሆነዋል

የፎቶው ባለመብት, Barcroft Media
በደቡባዊ ሜክሲኮ ነዋሪ የሆኑት ወላጆች የልጆቻቸው ማቆያ ሎተሪ ማሸነፉን በሰሙ አመፀኞች ምክንያት ሰላም ማጣታቸው ተሰማ።
ሕፃናት ማሳደጊያው 20 ሚሊዮን ፔሲ፤ በዶላር ሲመነዘር 950 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሎተሪ እንደደረሰው ተነግሯል።
ከ20 በላይ ሕፃናት ማቆያ የሆነው ሥፍራ ያሸነፈው የሎተሪ ገንዘብ በወላጆች እንዲተዳደር ተወስኗል።
ነገር ግን የሕፃናት ማቆያው ሎተሪ ማሸነፉ ከተሰማ በኋላ የታጠቁ ቡድኖች ለወላጆች ማስፈራሪያ መላክ ጀምረዋል።
ታጣቂዎቹ የሚሉት በሎተሪው ገንዘብ የጦር መሣሪያ ይገዛልን ነው።
ወላጆች በዚህ ማስፈራሪያ ምክንያት መኖሪያቸውን ለቀው መሸሻቸውና ኑሮ እንዳልተመቻቸው ተሰምቷል።
የወሮበሎች ጥቃት በተለመደባት ሜክሲኮ የታጠቁ ወንጀለኞች ሰላማዊ ነዋሪዎችን በመልመል እርስ በርስ ለሚያደርጉት ጦርነት ማዋል የተለመደ ነው።
‘ፕሌን ሎተሪ’ ተብሎ የሚጠራው ሎተሪ 500 ፔሶ የሚሽ ሲሆን ይህን አሸናፊ ቲኬት ገዝቶ አቅም ለሌላቸው ትምህርት ቤቶችና የሕፃናት ማቆያዎች የሚለግሰው አንድ ስሙ የማይጠቀስ ግለሰብ ነው።
ይህንን ሎተሪ ያሸነፉ 100 ሰዎች ስም ይፋ የሆነው ባለፈው ዓመት መስከረም ነበር።
ከእነዚህ ዕድለኞች መካከል ኦኮሲንጎ መንደር የሚገኝ አንድ የሕፃናት ማቆያ አንዱ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህን ዜና የሰሙ የሕፃናቱ ወላጆች መጀመሪያ በደስታ ቢፈነጥዙም የኋላ ኋላ ግን ሎተሪው ሳይደርሰን በቀረ ሳይሉ አልቀሩም።
የወላጆች ማኅበር አባላት ሎስ ፔቱልስ ከተሰኘው ታጣቂ ቡድን ማስፈራሪያ እየደረሳቸው እንደሆነና ቡድኑ የሎተሪው ገንዘብ ለመሣሪያ መግዣ እንዲውል እየጠየቀ እንዳለ ተናግረዋል።
ይህ ታጣቂ ቡድን ከጎረቤት መንደር ያለ አንድ ተቀናቃኝ ቡድንን ለማጥቃት ነው በሎተሪው ገንዘብ መሣሪያ ይገዛልኝ ያለው።
ቢሆንም ወላጆች የቡድኑን ጥያቄ ችላ በማለት ለሕፃናቱ ማቆያ አዲስ ጣራ እንዲገነባ ወስነዋል።
የታጣቂ ቡድኑ ማስፈራራት የበረታው ወላጆች የቀረውን 14 ሚሊዮን ፔሶ የመንደሯን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሳካት ማሰባቸው መሰማቱን ተከትሎ ነው።
ባለፈው መጋቢት ታጣቂዎች ገንዘቡን ካላመጣህ በሚል አንድ አባትን በጥይት መምታቸው ተሰምቷል።
በዚህ ያላበቁት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ባለፈው ወር ሕፃናትና ሴቶች ላይ ባደረሱት ጥቃት ምክንያት 28 ቤተሰቦች አካባቢውን ለቀው ተሰደዋል።
አንድ የወላጆች ማኅበር አባል አብዛኛው የመንደሯ ነዋሪ የቤት ንብረትና የቤት እንስሳት እንደተዘረፉ ተናግረዋል።
የወላጆች ቃል አቀባይ የሆኑ ሰው ጉዳዩን ለአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳስታወቁ፤ ታጣቂው ቡድን አንድ ካልተባለ ወደ መንደሯ እንደማይመለሱ አስታውቀዋል።












