የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር፡ እስራኤል ኢራንን ልታጠቃ ትችላለች የሚለው ስጋት ጨምሯል

ባለፈው ወር ከእስራኤል የወደብ ከተማ ኢላት በስተሰሜን ከሚገኘው አየር ማረፊያ ላይ ወታደራዊ ልምምድ ተደርጓል

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከቀናት በፊት ቀይ ባህር ላይ የእስራኤል፣ የኤምሬትስ እና የባህሬን ባህር ኃይሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአሜሪካ የጦር መርከብ ጋር በጋራ ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል።

ልምምዱ ባለፈው ወር ከእስራኤል የወደብ ከተማ ኢላት በስተሰሜን ከሚገኘው አየር ማረፊያ ላይ የተደረገውን ወታደራዊ ልምምድ ተከትሎ የመጣ ነው። በዚህም ከእስራኤል እና ከሌሎች ሰባት አገራት የተውጣጡ ተዋጊ አውሮፕላኖች ሰማይ ላይ ሲያጓሩ ታይተዋል።

የልምምዶቹ ዓላማ በቅርብ ጊዜ የራሷን ትልቅ ወታደራዊ ልምምድ ላደረገችው ኢራን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት እና ጠንካራውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳየት ያለመ ነው።

የእስራኤል ታጣቂ ኃይል በኢራን ኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ሊሰነዝር ለሚችለው ጥቃት መንግሥት 1.5 ቢሊዮን ዶላር መድቧል። ከፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች ዕለታዊ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው።

ምን ሊፈጠር እንደሚችል የኢራንን ጉዳይ የሚከታተሉ እና ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አንድ የእስራኤል የደህንነት ባለሥልጣን "እስራኤል ከኢራን ጋር ጦር ለመማዘዝ ምንም ፍላጎት የላትም። ሆኖም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድትታጠቅ አንፈቅድም። ከኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ግስጋሴ ጎን ለጎን ወታደራዊ አቅምን ጨምሮ ለሁሉም አማራጮች እየተዘጋጀን ነው" ብለዋል።

ኅዳር 29 በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና ኢራን እና በአምስት በዓለም ኃያላን መንግሥታት (አሜሪካ ደግሞ በተዘዋዋሪ) መካከል የ2015 የኒውክሌር ስምምነትን እንደገና ለማስጀመር የሚያልም ድርድር ሊደረግ ታቅዷል። .

ስምምነቱ የኢራንን የኒውክሌር እንቅስቃሴ ከመገደብ ባለፈ ጣቢያዎቹን ለፍተሻ ክፍት በማድረግ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን በከፊል ለማንሳት የተወሰነ ነው። ሆኖም እአአ በ2018 የወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ሲሰርዙት የእስራኤል ይሁንታ ተችሯቸዋል።

አዲስ ውይይት የሚካሄድበት ቀን ከተቆረጠ በኋላ ኢራን 25 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ማበልጸግ እንደቻለች አስታውቃለች። ይህም ጥራቱ 60 በመቶ ሲሆን ለኒውክሌር ቦምብ ከሚያስፈልገው ደረጃ በታች ነው። ከ210 ኪሎ ግራም በላይ የሚሆነውን ደግሞ 20 በመቶ ጥራት ማበልጸጓን አስታውቃለች።

ቴህራን ኒውክሌርን ለሰላማዊ አገልግሎት እንደምትጠቀም ትገልጻለች። የኢራን ባለሙያዎች ጭምር ግን በዚህ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም ቀደም ሲል በኒውክሌር የታጠቁ መንግሥታት ብቻ ይያዝ እንደነበር ጠቁመዋል።

የእስራኤል የደህንነት ባለሥልጣን "ዛሬ ኢራናውያን ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ የሚሆን ቁስ ለመፍጠር በፊት ከነበሩት አሁን የበለጠ ተቃርበዋል። ይህ እውነታ ደግሞ በእስራኤል መንግሥት ላይ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት መልዕክት አለው" ብለዋል።

ኢራን ይህን ለማድረግ ከወሰነች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለአንድ የኒውክሌር መሳሪያ የሚበቃ ዩራኒየም ማከማቸት እንደምትችል የእስራኤል መከላከያ ተቋም ግምቱን አስቀምጧል።

እንዲህ ዓይነቱን መሣሪያ ለመሥራትም በባለስቲክ ሚሳኤል ላይ ሊገጠም የሚችል መሣሪያን መሥራትን ይጠይቃል። ለዚህ የሚያስፈልገውን ጊዜ ለማስላት በጣም ከባድ ቢሆንም አንዳንድ ባለሙያዎች ከ18 እስከ 24 ወራት ሊፈጅ ይችላል ይላሉ።

ስለጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ ግልጽ ያልሆነ ፖሊሲ ያላት እና የራሷ የሆነ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት የምትገመተው እስራኤል እንደምትለው ከሆነ የኢራን የኒውክሌር ባለቤትነትን እንደህልውና ስጋት ነው የምትመለከተው። ኢራን በበኩሏ ለእስራኤል መንግሥት ዕውቅና አትሰጥም።

እስራኤል ጋር ግንኙነታቸው እያደገ ያለው የአሜሪካ እና የአረብ ባህረ ሰላጤ አገራት የኢራንን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት አጥብቀው ይቃወማሉ። ቢሆንም ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለው ድጋፍ ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

በእየሩሳሌም የስትራቴጂ እና የፀጥታ ተቋም ባልደረባ የሆኑት የቀድሞ የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ያኮቭ አሚድሮር በ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ነው የኢራንን የኒውክሌር ፍላጎት ስጋት ሲገልጹ የቆዩት።

በቅርቡ የተደረጉ ሁኔታዎችንም ገምግመዋል።

"ኢራናውያን ወደ ቦምቡ እየተቃረቡ በሚሄዱበት ሁኔታ ውስጥ እስራኤል አትኖርም። ስለሆነም እንዴት እንደምታስቆም በቅርቡ ውሳኔ መሰጠት አለበት" ብለዋል ።

"ኢራናውያን ከዛሬው የበለጠ ጠበኛ ከሚሆኑበት የኒውክሌር ባለቤትነት የሚመለሱ ባለመሆናቸው ጥቃት ከመፈጸም ውጭ ሌላ መንገድ አላይም" ይላሉ።

የኢራን ፕሬዚደንት ኢብራሂም ራሲ ( በግራ በኩል) በኢራን ቡሸር የኒዩክሌር ማበልፀጊያ ቦታ ንግግር ሲያደርጉ ( ጥቅምት 2021)

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ሁል ጊዜ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሆነ ትናገራለች

እስራኤል የጠላቶቿን የኒውክሌር ማመንጫዎችን ለማጥፋት እአአ በ1981 በኢራቅ እና በ2007 ደግሞ በሶሪያ ሁለት ጊዜ ብቻዋን ሞክራ ነበር።

ነገር ግን ብዙ ተንታኞች የኢራንን እጅግ የላቀ የኒውክሌር መርሃ ግብርን ለማስቆም ውስብስብ ኦፕሬሽን በተሳካ ሁኔታ መካሄድ መቻሉን ይጠይቃሉ። ምክንያቱ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች እና በመሬት ውስጥ ያሉ በርካታ ጣቢያዎችን በማካተቱ ስለሚከፈለው ዋጋ ይጠይቃሉ።

አሚድሮር እንደሚሉት "በእስራኤል የሚገኝ ሁሉም ሰው [ጥቃት ቢፈጸም] ወደ ውስብስብ ጦርነት እንደሚያመራ ይገነዘባል።"

ኢራን በበኩሏ እንዲህ ላለው ጥቃት "አስደንጋጭ ምላሽ" ለመስጠት ቃል ገብታለች። የራሷን ኃይል ከመጠቀም ባለፈ በአካባቢው ተሰራጭተው ከሚገኙት የታጠቁ ወዳጆቿ ጋር የተቀናጀ ጥቃት ልትወስድ ትችላለች ተብሎ ይገመታል።

በሊባኖስ የሚገኘውና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች ያለው ሂዝቦላህ፣ በሶሪያ እና ኢራቅ የሚገኙ የሺዓ ሚሊሻዎች፣ የየመን አማጺው ሁቲ እና በጋዛ ሰርጥ የጂሃድ ታጣቂዎች አብረዋት ሊሰለፉ ይችላሉ።

በእስራኤል ውስጥ ያሉ አንዳንድ የጦር ባለሙያዎች ምንም እንኳን ጥቃቱ ከባድ መዘዞች ቢኖሩትም የኢራን የኒውክሌር ዕቅዶችን በጥቂት ዓመታትም ቢሆን ወደ ኋላ ስለሚያጓትተው ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ያሰላሉ።

በይፋ የተገለፀው አማራጭ ግን አሁንም ሰላማዊ የድርድር መፍትሔዎችን ማስፋት ነው።

የቀድሞ የሞሳድ የስለላ ድርጅት የምርምራ ኃላፊ ሲማ ሺን "የዲፕሎማሲው መንገድ እንደሚሳካ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን ትልቅ ዕድል አልሰጠውም" ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለኢራን ወደ ስምምነቱ በቀጥታ እንድትመለስ ሃሳብ ቢያቀርቡም የእስራኤል መንግሥት ግን ተቃውሞታል።

ስምምነቱ እስከ 2025 ድረስ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ብዙ ገደቦችን ያነሳል። የኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል መርሃ ግብር ላይም ገደብ አላስቀመጠም። በአካባቢው ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች የምታደርገውን ድጋፍም አልገታም።

አሁን በእስራኤል የብሔራዊ ደህንነት ጥናት ተቋም የኢራን ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ሺን "በኢራን አቋም ላይ ያለኝ ግምገማ ወደ ኋላ መመለስ እንደማትፈልግ ነው" ብለዋል።

"እርግጥ ማየት የሚፈልጉት የማዕቀብ መላላት ነው። እሱን ለማግኘት አንድ ነገር መክፈል እንዳለባቸው ተረድተዋል ። ጥያቄው የኢራን ስሌት ምንድነው? ኢኮኖሚዋ ምን ያህል እፎይታ ይፈልጋል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ፍርሃታቸውም አገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የላቁ የበለፀጉ የዩራኒየም ክምችቶችን ለመያዝ የኒውክሌር ውይይቶቹ ጊዜ መግዣ መንገድ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ነው።

ዋሽንግተን በሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ኢንስቲትዩት የኢራን ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አሌክስ ቫታንካ በበኩላቸው ቴህራን ለኒውክሌር መርሃ ግብሯ ያላትን ጥልቅ የርዕዮተ ዓለም ቁርጠኝነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአውሮፓውያን እና በአሜሪካ ላይ እምነት ባይኖራቸውም የአገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ለማቃለል ወደ ውይይቱ መመለስ እንደምትፈልግ ያምናሉ። የሰሞኑን ተግባራቷ እና ጥያቄዎቿ "እጇን እንደሚያጠናክር" ነው የሚመለከቱት።

ኢራን የግድ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን እንደማትፈልግ ቫታንካ ይናገራሉ።

"ይህ በግልጽ እንዲኖራቸው የሚፈልጉት አማራጭ ነው። ነገር ግን ጉዳዩ የጦር መሳሪያ ስለመያዝ አይደለም" በማለት ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ልትቆይ እንደምትችል ይገልጻሉ።

"ጉዳዩ ኢራን ወሳኝ የኒውክሌር አገር ስለመሆኗ እና የሥርዓት ለውጥ እንደማይመጣ ለአሜሪካውያን ማሳየቱ ነው" ብለዋል።

የእስራኤል የጥቃት ዛቻ አያሳምናቸውም።

ቫታንካ አክለውም "ይህን ማድረግ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። ኢራን በከፍተኛ ደረጃ በግልጽ ሙሉ በሙሉ ሰርጋ ገብታለች። በእርግጠኝነት እነሱ ያላቸው የመረጃ ፍሰት አላቸው" ብለዋል።

ከአስር ዓመታት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል በመቀናጀት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማደናቀፍ የስቱክስኔት ኮምፒዩተር ቫይረስን በመጠቀም ጥቃት መሰንዘሩ ሪፖርት ተደርጓል።

ኢራን በቅርቡ በቴህራን አቅራቢያ በርቀት መቆጣጠሪያ በታገዘ መሣሪያ በከፍተኛ የኒውክሌር ሳይንቲስቷ ሞህሰን ፋክሪዛዴህ ላይ ለደረሰው ግድያ እና በኒውክሌር ተቋሞቿ ላይ በተፈጸሙ ፍንዳታዎች እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች።

"በጦርነቶች መካከል ጦርነት" ብላ እስራኤል በሰየመችውና በመቶዎች በሚቆጠሩ ወታደራዊ ጥቃቶቿ በኢራን በጎረቤት ሶሪያ ያላትን እንቅስቃሴ ለማሰናከል እና ሂዝቦላህ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን አድርጋለች።

የመስፋፋት ፍርሃት

በቀጣይ ስለሚሆነው ነገር በባለሙያዎች መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ። በቅርቡ በኢራን የኒውክሌር እቅድ ላይ የሚደረጉ ንግግሮች ወሳኝ በሆነ ጊዜ ላይ መምጣታቸውን እና የቀጠናው የጦርነት ስጋት ከፍ ሊል እንደማይችል የጋራ መግባባት አለ።

ኢራን የራሷን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ካመረተች እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና ግብጽ ያሉ አገራትም ይሄንኑ ሊከተሉ ይችላሉ።

ዋሽንግተን በመካከለኛው ምስራቅ የሚካሄደውን "ዘላለማዊ ጦርነቶች" ማስቆም እንደምትፈልግ ተናግራለች። ኢራንን በተመለከተ ግን "ሌሎች አማራጮችን" እንደምትመለከት አስጠንቅቃለች።

በቅርቡ የተደረገው የእስራኤል የአየር ልምምዱ ሲጠናቀቅ ከመሬት በታች የኒውክሌር ቦታዎችን ለማጥቃት የሚያገለግል ቦምብ መሸከም የሚችል የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን በእስራኤል አየር ክልል በኩል በሁለት የእስራኤል ተዋጊ ጄቶች ታጅቦ ታይቷል።