የመኒ-ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል በሁቲ አማጺያን የአምስት ዓመት እስር ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, Intisar al-Hammadi
ከኢትዮጵያዊት እናት እና ከየመናዊ አባት የተወለደችው የ20 ዓመቷ ሞዴል እና የፊልም ከያኒ ኢንቲሳር አል-ሃማዲ "ግብረገብነት የጎደለው ተግባር በመፈጸም ብሎም አደንዛዥ ዕጽ በመያዝ" ወንጀሎች ጥፋተኛ መባሏን ሳባ የተሰኘው በሁቲ አማጺያን የሚመራው የዜና ወኪል ዘገበ።
ኢንቲሳር እንዲሁም አንዲት ከሦስት ዓመት በፊት የታሰረች ሴት የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ለሦስት እና አንድ ዓመት የታሰሩ ሁለት ሴቶች መኖራቸውም ተዘግቧል።
ኢንቲሳር ከሞዴሊንጉ ባሻገር በሁለት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ የተሳተፈች ሲሆን ፀጉሯን ሳትሸፍን የተነሳቻቸው ፎቶዎች በበይነ መረብ ላይ ይሰራጩ ነበር።
ባለፈው የካቲት ወር በሰንአ ከተማ የታሰረችው ግለሰቧ ከታሰረች በኋላ በሁቲ ኃይሎች የቃላት ብሎም አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባት ተናግራለች።
ኢንቲሳር በእስር ቤት ውስጥ ሳለች እንዲጎበኟት ለተፈቀደላቸው ጠበቆች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዓይኗን ተሸፍና ስለፈረመችው ሰነድ ገልጻለች።
ሰነዱም ለተለያዩ ወንጀሎች የተሰጠ የእምነት ቃል መሆኑ ተነግሯል።
በቁጥጥር ስር ከዋለች ከአንድ ወር በኋላም ወደ ሰንዓ ማዕከላዊ እስር ቤት የተዘዋወረች ሲሆን ከጠባቂዎቹም "ጋለሞታ" እንዲሁም ከኢትዮጵያዊ በመወለዷ እና ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ስላላት "ባሪያ" የሚሉ ስድቦችን ማስተናገዷን ጠበቃዋ ተናግረዋል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ጉዳዩ "አግባብነት የሌለው አሰራርን ከጥቃት ጋር አጣምሮ የያዘ" ነው ሲል አውግዞታል። ድርጊቱንም "ፍትሃዊነት የጎደለው እንዲሁም በፖለቲካዊ አላማ የተነሳሳ" በማለት የተቋሙ የየመን አጥኚ አፍራህ ናስር በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
በሳዑዲ አረቢያ ከሚመራው ጥምር ጦር ድጋፍ ያላቸው የየመን መንግሥት እና ለመንግሥት ታማኝ የሆኑ ኃይሎች ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ከሁቲ አማጺያን ጋር እተዋጉ ሲሆን ሁቲዎች አብዛኛውን ምዕራባዊ የየመን ክፍሎችን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
የየመን የመረጃ ሚኒስትር ሞአማር አል-ኢሪያኒ ይህ ጉዳይ "የሁቲ ሚሊሻዎች በየመን ሴቶች ላይ የሚፈጽሟቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀሎች ማሳያ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
የተከሳሽ ሴቶቹ ጠበቃ ካሊድ አል-ከማል በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
ጠበቃው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ለሂውማን ራይትስ ዋች እንደገለጹት ኢንቲሳር እና ጓደኞቿ በሰንዓ ከተማ በመኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር የሁቲ ሚሊሻ አባላት አስቁመው በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው።
"ስልኳን በመውረስ ለሞዴሊንግ ሥራ የተነሳቻቸው ፎቶዎች እንደ ለግብረገብነት ተቃራኒ እንደሆኑ ከመቁጠራቸው ባሻገር በሁቲ ሃኃፊዎች ዘንድ በወሲብ ንግድ እንደሚተዳደር ሰው ተቆጥራለች" ሲሉም ተናግረው ነበር።












