የፈረንሳዩ ማክሮን የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ዋሽቶኛል አሉ

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ነጭ ውሸት እንደተዋሹ ለጋዜጠኞች ተናገሩ፡፡

ማክሮን በጋዜጠኛ፣ ‹ሞሪሰን የዋሸዎት ይመስሎታል ወይ?› ተብለው ሲጠየቁ፣ ‹ይመስለኛል ሳይሆን ዋሽቶኛል እንጂ› ብለው ጠጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ መሻከር የተከሰተው አውስትራሊያ በኒውክሊየር የሚንቀሳቀሱ እጅግ ዘመናዊ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦች እንዲኖሯት ከፈረንሳይ የነበራትን ወታደራዊ ስምምነት ሰርዛ ወደ አሜሪካ ፊቷን በማዞሯ ነው፡፡

የፈረንሳዩ ማክሮን አገራቸው ፈረንሳይ ከአውስትራሊያ ጋር የነበራት የ37 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መሰረዙ እጅግ አበሳጭቷቸው ከርሟል፡፡

ስምምነቱ ፈረንሳይ ለአውትስራሊያ 12 ባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን እንድትገነባላት የሚያደርግ ነበር፡፡

ነገር ግን አውስትራሊያ ይህን የጸና ስምምነት ቸል በማለት አዲስ ስምምነት ከአሜሪካና ከዩኬ ጋር ተፈራርማለች፡፡ ይህ የሦስትዮሹ ስምምነትም አውከስ (Aukus) በሚል ምሕጻር ይጠራል፡፡

አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን ስምምነት መሰረዟ ከፍተኛ ቁጣን የፈጠረ ሲሆን የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድርጊቱን ‹‹በወዳጅ ከጀርባ በስለት የመወጋት ያህል ነው›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የስምምነቱን መታጠፍ ተከትሎም ፈረንሳይ አምባሳደሮቿን ከአሜሪካና ከአውስትራሊያ እንድትጠራ አስችሏት ነበር፡፡

ጆ ባይደን ይህ መቃቃር ከተፈጠረ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈው አርብ ማክሮንን በአካል ያገኟቸው ሲሆን ለተፈጠረው ነገርም ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡

አውስራሊያ በኒውክሊየር የሚዘወር ባሕር ሰርጓጅ ወታደራዊ መርከብ ያስፈለጋት ቻይና በአካባቢው ያላት ኃያልነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገዘፈ መሄዱ ነው፡፡

በዓለም ላይ እንዲህ የተራቀቀ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ያላቸው አገራት 6 ብቻ ናቸው፡፡