ቻይና ከትምህርት ቤት ለልጆች የሚሰጥ የቤት ሥራ ጫናን የሚቀንስ ሕግ አወጣች

ቻይና በትምህርት ቤት ለተማሪዎች የሚሰጥን ከመጠን በላይ የቤት ሥራ እና ከትምህርት ቤት ሰዓት ውጪ የሚሰጥ የጥናት ፕሮግራምን ለመቀነስ ያለመ ሕግ ማውጣቷ ተዘገበ።

ወላጆች ልጆቻቸው በቂ የእረፍት እና የጨዋታ ጊዜ እንዲኖራቸው እንዲሁም በኢንትርኔት ላይ ብዙ ሰዓት እንዳያጠፉ እንዲቆጣጠሩም ተጠይቀዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ቻይና ለስድስትና ለሰባት ዓመት ተማሪዎች በትምህርት ቤት የጽሑፍ ፈተና እንዳይሰጣቸው አግዳለች።

ባለሥልጣናት ተማሪዎች በሚደርስባቸው ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጫና ምክንያት ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳት እየገጠማቸው ነው ብለዋል።

በልጆች ላይ የሚስተዋለውን የኢንተርኔት እና ተያያዥ ሱሶችን ለመቆጣጠር ባለፈው ዓመት የቻይና መንግሥት በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል።

በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችለውን የአሁኑን ውሳኔ ያሳለፈው የቻይና ዋነኛ ሕግ አውጪ አካል የሆነው የብሔራዊው ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ነው።

የአዲሱ ሕግ ሙሉ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም የቻይና መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ወላጆች የልጆቻቸውን ሞራል እንዲገነቡ፣ ዕውቀታቸውንና ማኅበራዊ ልማዳቸውን እንዲያዳብሩ እንዲያግዙ ይጠይቃል።

ይህ የመንግሥት እርምጃ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተደበላለቀ ምላሽ እያገኘ ነው። አንዳንዶች እርምጃው ለመልካም የልጆች አስተዳደግ የሚበጅ መሆኑን ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ አካባቢያዊ መስተዳደሮች ወይም ወላጆች ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ባላቸው ብቃት ላይ ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ቻይና በኢንተርኔት አማካይነት በዋና ዋና የትምህርት ዓይነቶች ዙሪያ የሚሰጡ ትምህርቶች በአገሪቱ እንዳይሰጡ አግዳለች።

አዲሱ የመንግሥት እርምጃ በዘርፉ በሚካሄድ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ እገዳን የሚጥል ሲሆን 120 ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበትን በግሉ ዘርፍ የሚካሄድ ትምህርትንም ክፉኛ ይጎዳዋል ተብሏል።

በቻይና ውስጥ በዜጎች መካከል ያለው የትምህርት ተደራሽነት ፍትሐዊነት ላይ ጥያቄ የሚነሳ ሲሆን፣ ሀብታም ወላጆች ልጆቻቸው በዋነኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲማሩ ከፍተኛ ገንዘብ ከማውጣት ወደኋላ እንደማይሉ ሪፖርቶች አመልክተዋል።