የኮሮናቫይረስ ክትባት አልወስድም ያሉት የእግር ኳስ አሰልጣኝ ከሥራ ተባረሩ

በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ የእግር ኳስ አሰልጣኝ የነበሩት ኒክ ሮሎቪች የኮሮናቫይረስ ክትባት አልወስድም በማለታቸው ከሥራ ተባረሩ።

ታዋቂው አልጣኝ ኒክ በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ተከፋይ ነበሩ። እሳቸውን ጨምሮ አራት ተባባሪ አሰልጣኞችም የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመውሰድ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከሥራ ተሰናብተዋል።

ዋሽንግተን ውስጥ የመንግሥት ተቀጣሪዎች ክትባቱን መውሰድ ግዴታቸው ነው። የማይከተቡ ሰዎች ከሥራ እንደሚባረሩም ተደንግጓል።

የ42 ዓመቱ አሰልጣኝ ኒክ በዓመት 3.1 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላቸው ነበር። ክትባቱን አልወስድም ያሉት 'ሐይማኖቴ አይፈቅድም' በሚል ምክንያት ነው።

የዩኒቨርስቲው የአትሌቲክስ ዳይሬክተር ፓት ቻን እንዳሉት ሐይማኖትን ሰበብ አድርጎ ክትባት አለመከተብ የተከለከለ ነው።

የአሰልጣኙ መባረር የእግር ኳስ ቡድኑን ቢጎዳም "ቅድሚያ የምንሰጠው ለተጫዋቾቹ ጤና ነው" ብለዋል።

ዴሞክራቱ የዋሽንግተን አገረ ገዢ ጄይ ኢንሲል ባለፈው ነሐሴ ላይ ነበር የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመንግሥት ተቀጣሪዎች ግዴታ ያደረጉት።

አሰልጣኙ ግን በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ክትባቱን ሳይወስዱ ቀርተዋል።

"የግል ውሳኔዬ ነው። ማንኛውም አሰልጣኝ፣ ተማሪ ወይም አትሌት ክትባቱን በተመለከተ የሚወስደውን የግል ውሳኔ አከብራለሁ" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ኒክ ሮሎቪች ክትባት አልወስድም በማለት ሥራቸውን ያጡ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የመጀሪያው አሰልጣኝ ናቸው።

ከዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርስቲ ሠራተኞች 90 በመቶው፣ ከተማሪዎች መካከል ደግሞ 97 በመቶው መከተባቸው ተገልጿል።