ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናው ፕሬዝዳንት ከታይዋን ጋር 'እንዋሃዳለን' አሉ
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የቻይና እና የታይዋን "ውህደት እውን መሆን አለበት" ሲሉ ተናገሩ አሉ።
ቻይና እና ታይዋን በሰላማዊ መንገድ መዋሀድ አለባቸው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። ነገርግን የቻይና ሕዝቦች መነጣጠልን የማይደግፍ "ድንቅ ባህል" እንዳለው ተናግረዋል።
የታይዋን ፕሬዝዳንት የግዛቲቱ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በሕዝቧ ብቻ ነው ማለታቸውን ተከትሎ ነው ዢ ጂንፒንግ "እንዋሀዳለን" ያሉት።
ታይዋን እራሷን እንደ አንድ ሉአላዊ አገር የምታይ ሲሆን፣ ቻይና ደግሞ ታይዋን ተገንጥላ የወጣች የግዛቷ አካል እንደሆነች ታምናለች።
ቻይና ከታይዋን ጋር ለመዋሀድ የምታደርገው ጥረት ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃን ሊያካትት ይችላል ተብሎ ይታመናል።
ባለፈው ሳምንት 150 የቻይና ተዋጊ ጀቶች በታይዋን የአየር ክልል ውስጥ መታየታው በቻይና እና ታይዋን መካከል ያለውን ውጥረት አባብሷል።
አሜሪካ ይህ ውጥረት "እጅግ አስግቶኛል" ማለቷም አይዘነጋም።
ቻይና እአአ በ1911 ንጉሣዊ ሥርወ መንግሥት በአብዮት የጣለችበት 110ኛ ዓመት እየተከበረ ይገኛል።
ይህንን ክብረ በዓል አስመልክቶ ዢ ጂንፒንግ ባደረጉት ንግግር ላይ ከታይዋን ጋር ስለመዋሀድ አንስተዋል።
ባለፈው ሐምሌ ላይ ታይዋን ነጻ አገር ነኝ ብላ ለማወጅ የምታደርገውን ጥረት "እናከስማለን" ብለው ነበር። "የእናት አገር ቻይና ግዛቶች መዋሀዳቸው አይቀርም" ሲሉ ተደምጠዋል።
የቻይና ፍላጎት ታይዋንን እንደ ሆንግ ኮንግ ማድረግ ነው። ይህ ማለት አንድ አገር ሆነው ሁለት የአመራር ሥርዓት ይኖራል ማለት ነው።
ዢ ጂንፒንግ ባደረጉት ንግግር "ታይዋንን ራስ ገዝ የማድረግ ንቅናቄ ከእናት አገር ግዛት ጋር እንዳትዋሀድ ያደናቅፋል። ለብሔራዊ ደኅንነትም ስጋት ነው" ብለዋል።
የታይዋን ፕሬዝዳንት ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ አንድ አገር ሁለት የአመራር ሥርዓትን ሕዝቡ አይደግፍም ብሏል።
ቻይና "ጠብ አጫሪ ጣልቃ ገብነቷን እና ትንኮሳዋን ብታቆም ይሻላታል" ሲልም መግለጫው ያትታል።
የቻይና እና የታይዋን ፍጥጫ
በቻይና እና በታይዋን መካከል ያለው ግንኙነት ከሻከረ ሰነባብቷል።
እአአ በ1940ዎቹ የተነሳ የእርስ በእርስ ጦርነትን ተከትሎ ነበር ለሁለት የተከፈሉት።
ቻይና በውዴታም ይሁን በግዴታ ታይዋን ተመልሳ የቻይና ግዛት እንድትሆን ትፈልጋለች። ደሴቷ ታይዋን ይህንን የቻይና አቋም በፍጹም አትቀበልም።
ታይዋን የራሷ ሕገ መንግሥት፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተመረጡ መሪዎች እና 300,000 ገደማ ወታደሮች አሏት።
ታይዋንን እንደ ነጻ አገር የተቀበሉ አገሮች ውስን ናቸው። በርካታ አገሮች ታይዋንን የቻይና ግዛት አድርገው ነው የሚወስዱት።
አሜሪካ ከታይዋን ጋር ይፋዊ ግንኙነት የላትም። ነገር ግን ደሴቷ ራሷን መከላከል እንደምትችል የሚጠቁም ድንጋጌ አላት።
ቻይና እና ታይዋን በታሪክ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የገቡት እአአ በ1996 ነው። ያ ወቅት ቻይና የታይዋንን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማሰናከል በሚል የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችበት ወቅት ሲሆን፤ አሜሪካ ወደ አካባቢው የቶር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿን በማሰማራት ነገሩን አብርዳዋለች።
ብዙ የአውሮፓ አገራት፤ ቻይና ኃይል ለመጠቀም ማስፈራራቷን ኮንነዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ዢ ጂንፒንግ "በታይዋኑ ስምምነት ለመመራ ተስማምተዋል" ብለዋል።
አሜሪካ "የታይዋን ስምምነት" የምትለው ድንጋጌዋ እውቅና የሚሰጠው ለቻይና ብቻ ነው። ይህም ታይዋንን ችላ ያለ ነው።
ይህ ድንጋጌ ለቻይና እውቅና ይስጥ እንጂ አሜሪካ ከታይዋን ጋር "ይፋዊ ያልሆነ" ግንኙነት እንድትመሠርት ይፈቅዳል።
አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሣሪያ ትሸጣለች። ታይዋን እራሷን መከላከል ካስፈለጋት አሜሪካ የመደገፍ መብት እንዳላትም በድንጋጌው ሰፍሯል።