ለላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ልደት ትልልቅ ሰሌዳዎች መሰቀላቸው አነጋጋሪ ሆኗል

የላይቤሪያው ፕሬዘዳንት ጆርጅ ዊሃ 55ኛ ልደት በአል መቃረብን ተከትሎ ዋና ከተማዋ ሞኖሮቪያ በትልልቅ የመልካም ልደት መግለጫ ቢልቦርዶች ተሞልታለች።
ከሁለት ቀናት በኋላ ልደታቸው የሚያከብሩት ፕሬዘዳንቱ እነዚህ ሰሌዳዎች እየቆሙላቸው የሚገኘው በሞኖሮቪያ ከተማ ምክርቤት ሲሆን በተለይም በማዕከላዊ ሞኖሮቪያ በብዛት ተሰቅለው ታይተዋል።
አሁንም በርካታ ቢልቦርዶች በመሰቀል ላይ ሲሆኑ ሁሉም ሰሌዳዎቹ ተመሳሳይ መልክት ይዘዋል።
«ሁሉም መሪዎች እርስዎን መሆን አለባቸው። ምክኒያቱም እርስዎ የብቃት ፍጹም ምሳሌ ስለሆኑ። መልካም ልደት አለቃ። በልቦት ውስጥ የተሸሸጉት ህልሞችዎ እውን ይሁንልዎት» ሲል በቢልቦርዶቹ ላይ የተከተበው መልዕክት ይነበባል።
የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ፕሬዚዳንቱ ይህ ይገባቸዋል የሚሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። የመሪያቸውን ፎቶ በመላው ከተማዋ በመመልከታቸው ደስተኞች ናቸው።
ነገር ግን የፕሬዘዳንቱ ተቺዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። በኢኮኖሚ ቀውሶች ውስጥ የምትገኘው ላይቤሪያ አብዛኛው ህዝቧ ድሀ ሆኖ እያለ ቢልቦርዶቹ ይዘውት የወጡት መልዕክት ግን ግዴለሽነትን ያንጸባርቃል ሲሉም ተችተዋል።
የሞኖሮቪያ ከንቲባ ጄፈርሰን ኮጄም ቢሆኑ በቅርቡ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ልደታቸውን ድል አድርገው አክብረዋል። ደጋፊዎቻቸው የአደባባይ ትርኢት ጭምር አቅርበዋል። የእርሳቸውም ምስሎች በትልልቅ ሰሌዳዎች በሞኖረቪያ ጎዳናዎች ላይ ተሰቅለው ታይተው ነበር።








