በአመጽ የተሳተፉ የትራምፕ ደጋፊዎችን እስር የሚቃወም ሰልፍ በካፒቶል ተካሄደ

ሰልፉን የሚቃወሙ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከጥቂት ወራት በፊት የካፒቶል ህንፃን ያጠለፉትን የትራምፕ ደጋፊዎችን አመፅን ለመደገፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቅዳሜ እለት በካፒቶል ሰልፍ አድርገዋል።

ሆኖም ሰልፈኞቹ በስፍራው ከተሰማራው የጸጥታ ሀይልና የሚዲያ ባለሙያዎች ያነሰ ቁጥር ያላቸው ናቸው።

ከሰልፉ ቀደም ብሎ ፖሊስ አመፅ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል መረጃዎች በማግኘቱን በዋሽንግተን ጥበቃው እንዲጠናከር ተደርጎ ነበር።

የሰልፉ አስተባባሪዎች 700 ሰልፈኞችን ለማሳተፍ ፈቃድ ቢኖራቸውም ተሳታፊዎቹ ግን ከ200 እንደማይበልጡ ሮይተርስ ዘግቧል።

የካፒቶል ፖሊስ ከ 400 እስከ 450 ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንደነበሩ ገልጾ ይህ አኃዝ ግን በስፋት የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያጠቃልላል ብሏል።

የዋሽንግተን ፖሊስ ቀደም ብሎ በሰልፉ ስጋት እንዳለው ሲገልጽ ተሰምቷል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ መኮንኖች በካፒቶል ግቢ ውስጥ ሲዘዋወሩ የነበረ ሲሆን100 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ተጠባባቂ ሆነው ተሰማርተዋል።

የካፒቶል ዙሪያ በአጥር የተተከለ ሲሆን እና የምክር ቤቱ አባላት ከአካባቢውን እንዲርቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸውም ነበር።

በሰልፉ ንግግር ያሰሙ ሰዎች ባለፈው ጥር ወር ላይ በካፒታሎ በተፈጠረው ሁከት በቁጥጥር ስር የዋሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ምንም ዓይነት ሁከት ያልፈጠሩ "የፖለቲካ እስረኞች" እንደሆኑ አጥብቀው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የባለፈው የካፒቶል ተቃውሞ ላይ እንደተሳተፉ የተጠረጠሩ 600 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል።