አሜሪካ እጥላለሁ ያለችውን ማዕቀብ ለማዘግየት የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ ገለጸች

አንቶኒ ብሊንከን
የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን

በሠሜን ኢትዮጵያ በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭቱን ለማስቆም አስቸኳይ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ አሜሪካ ልትጥል ያሰበችውን ማዕቀብ ለማዘግየት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለሰላምና መረጋጋት እንቅፋት በሚሆኑ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ወይም የተኩስ አቁም እንዳይደረግ በሚያደናቅፉ እንዲሁም ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ ግለሰቦችና አካላት ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፈርመዋል።

ፕሬዝዳንቱ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተሰተውን ግጭት በተመለከተ እያራመደችው ያለውን አቋም በማንሳት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ ነች ያሏት አሜሪካ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምትከተለው ፖሊሲ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለሰብአዊነት ከመቆርቆር የዘለለ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዕቀባው የሚመለከታቸው አካላት ግጭቱን ለማስቆም በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም የሚያደርጉ ከሆነ የታሰቡት የማዕቀብ እርምጃዎች እንዲዘገዩ በማድረግ በድርድሩ ሂደት ላይ ለማገዝ ትኩረት እንደምታደርግ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዝዳንት ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ በዚህ ጦርነት ወቅት ዓለም በተሳሳተ ምክንያት ወቀሳና ትኩረቱን በኢትዮጵያ ላይ ማድረጉን በመግለጽ በአገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ቡድን ግን "በይፋ ተጠያቂ ለማድረግ አልቻለም" ሲሉ ወቅሰዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የአሜሪካ መንግሥት ከአጋሮቹ ጋር የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ቢያደርግም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልላዊ መስተዳደር እና ህወሓት ሰላማዊ መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም ብሏል።

በዚህም ምክንያት በግጭቱ ውስጥ ሚና ያላቸው አካላት ላይ የተለያዩ እቀባዎችን ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ በፕሬዝዳንቱ መፈረሙን ያመለከተው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ አሜሪካ ግጭቱን ለማስቆም ተገቢ የምትላቸውን እርምጃዎችን መውሰድ እንምትቀጥል ገልጿል።

መግለጫው የኤርትራ ሠራዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽሞታል ከሚባለው ከባድ የመብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት በኤርትራ መከላከያ ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በሆኑት በጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ የንብረት ዕገዳ መጣሏን አስታውሷል።

ቀደም ሲልም በሠሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ በሆኑና ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋሉ በተባሉ ግለሰቦች ላይ የቪዛ እገዳ እንዲጣል የሚያደርግ ትዕዛዝ መውጣቱ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ግጭቱን በማቆም ያለቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ተኩስ የማቆም ድርድር እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርቧል።

ጨምሮም በድርድር ላይ የተመሰረተው ተኩስ አቁም ለጦርነቱ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ወደሚያስገኝ ሰፊ ውይይት የሚያመራ መሆን እንዳለበት አመልክቶ፤ የኤርትራ ሠራዊትም ከኢትዮጵያ በአሰቸኳይና ለመጨረሻ ጊዜ መውጣት አለባቸው ብሏል።

ግልጽና ወደ ተኩስ አቁም በሚወስድ ሁኔታ የመብት ጥሰቶችን የሚያስቆሙ እርምጃዎችና የሰብአዊ እርዳታን ያለገደብ ለማድረስ የሚያስችሉ እርምጃዎች የማይታዩ ከሆነ ፕሬዝዳንቱ ያወጡት የማዕቀብ ውሳኔ የሚመለከታቸውን መሪዎች፣ ድርጅቶችና ሌሎች አካላትን ለይታ ታሳውቃለች ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ።

ነገር ግን ተገቢ የሰብአዊ ድጋፎች እንዲቀጥሉ የሚደረግ ሲሆን ለግለሰቦች የሚላክ ገንዘብ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና በመንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኩል የሚቀርቡ ምግብ እና መድኃኒቶች ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ መድረሳቸውን ይቀጥላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በደብዳቤያቸው ላይ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ ካካሄደችው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ላይ እየተፈጸመ ያለው ተገቢ ያልሆነ ጫና "አድሏዊ በሆነና መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተቃረነ ሁኔታ ማዛባትን መሠረት ያደረገ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአሜሪካ አስተዳደሮች በጥድፊያ በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት ከመፍትሄ ይልቅ በርካታ ሕዝቦችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጉን በመግለጽ "ኢትዮጵያ ከሚሊዮኖች ደኅንነት ይልቅ ሥልጣንን በሚያስቀድሙ ግለሰቦች ለተቀናበረ ግፊት አትንበረከክም" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ለፕሬዝዳንት ባይደን በጻፉት ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል።