ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያን የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ አየር መንገዱ ከቦይንግ ጋር ስምምነት ደረሰ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ይፋ ባደረገበት መግለጫ፤ ቦይንግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የአቪዬሽን መሪ መሆኑን እውቅና ሰጥቷል ብሏል።
የ70 ዓመታት ወዳጅነት ያላቸው ሁለቱ ተቋማት ከዚህ ስምምነት መድረሳቸው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአቪዬሽን አገልግሎት የመፍጠር ፍላጎታቸውን አመላካች ነው ተብሏል።
በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ሁለቱ ኩባንያዎች ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ በኢንደስትሪያል ልማት፣ በላቀ የአቪዬሽን ስልጠና፣ የትምህርት አጋርነት እና የአመራር ልማት በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አየር መንገዱ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከቦይንግ ጋር የተደሰረው ስምምነት "የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ማዕከል የመሆን ግብን ያሳካል" ብለዋል በመግለጫው ላይ።
የተደረሰውን ስምምነት ተፈጻሚ የሚያደርግ ከሁለቱ ኩባንያዎች የተወጣጣ ቡድን መቋቋሙም በአየር መንገዱ መግለጫ ላይ ተመልክቷል።
ቦይንግ ስምምነቱን በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነው።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ዓመታዊ እድገቱ 25 በመቶ እንደነበረ ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በቅርቡም አየር መንገዱ ባጓጓዘው የመንገደኞች ብዛት ከምርጥ 200 አየር መንገዶች 20ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ዓለም አቀፍ የትራንስፖርት ማኅበር አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ደረጃ ያገኘው ከ16 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች በማጓጓዝ ነው።
የዩናይትድ አረብ ኤምሬትሱ፤ ኤምሬትስ አየር መንገድ ከ78 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን በማጓጓዝ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የአየርላንዱ ራይንኤይር 64 ሚሊዮን ገደማ መንገደኞችን አጓጉዟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት በመቶዎች የሚቆጠሩ መዳረሻዎች ያሉት አየር መንገዱ 130 አውሮፕላኖች አሉት። ከእነዚህም መካከል እጅግ ዘመናዊ የሚባሉትን 16 ኤይርባስ ኤ350-900 እና 19- ቦይንግ ቢ787-8 ይጨምራል።
ቦይንግ
የአሜሪካው ቦይንግ የዓለማችን ቀዳሚ ኤሮስፔስ ኩባንያ እና የንግድ አውሮፕላኖች አምራች ኩባንያ ነው።
በ150 አገራት ደንበኞች አሉኝ የሚለው ቦይንግ፤ ከመንገደኞች አውሮፕላኖች በተጨማሪ፣ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ሳተላይቶችን፣ ጦር መሳሪያዎችን፣ የመከላከያ ሥርዓቶችን እና የኮሚዩኒኬሽን ሥርዓቶችን ያመርታል።