ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከጽዳት ሠራተኛነት የጌጣጌጥ ድርጅት እስከ መመስረት
እየሩሳሌም ቀንዓ የሊሉያን ድርጅት ባለቤት ናት። ሉልያን በፋሽን ጌጣጌጥ ምርቶች እንዲሁም በቆዳ ምርቶች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው።
ሊሉያን ለፋሽን እና ፕሮሞሽን የሚሆኑ እና ለገበያ የሚያቀርባቸውን ምርቶች በአጠቃላይ የሚሰራው ተመልሰው ጥቅም ላይ በሚውሉ እና አካባቢን የማይበክሉ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ነው።
እየሩሳሌምን ወደዚህ ሙያ የገፋት ልጅነቷ እና አስተዳደጓ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናግራለች።
እናቷ እና አባቷ ተለያይተው በእናቷ እጅ ያደገችው እየሩሳሌም፣ የእናቷን የእደጥበብ ሙያ ብቻ ሳይሆን የኑሮ ውጣ ውረዳቸውም በርካታ ነገሮችን እንድትቀስም አድርጓታል።
እናቷ እርሷን ሲያሳድጉ ቤት ውስጥ ብቻዋን ጥለዋት መውጣት ከባድ ፈተና ሆኖባቸው የነበሩባቸውን ጊዜያቶች ታስታውሳለች።
በልጅነቷ ወቅት ቤተሰቦቿ ከጎረቤት እንዲሁም ከሞግዚት ጋር ትተዋት በሄዱባቸው ወቅቶችም የተለያዩ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ ጥቃቶችን ማስተናገዷንም እንደዚሁ።
የእየሩሳሌን እናት የተመሰከረላቸው የእደ ጥበብ ባለሙያ ነበሩ።
ከልጅነቷ ጀምሮ የልብስ ቅድና ስፌት ሙያን ከእርሳቸው እጅ ተምራለች። በአራት ዓመቷም ከፌስታል ቦዲ መስራቷን ትናገራለች።
እርሷ ይህንን እውቀት ከእናቷ ከመውረሷ በፊት ግን ከአራት ዓመቷ ጀምሮ ለእርሳቸው እንደ ሞዴል በመሆን ለሚሰፏቸው ልብሶች መሞከሪያ እንደነበረች ትናገራለች።
ከእናቷ ያገኘችውን የእደጥበብ እውቀት ትሰራ የነበረው ግን እንደ ግል ተሰጥኦ በመውሰድ እንደነበር እየሩሳሌም ታስታውሳለች።
ከዚያ በኋላ ግን የኮሌጅ ትምህርቷን በምትማርበት ወቅት የተለያዩ ጌጣጌጦችን በመሥራትና በመሸጥ ገቢ ታገኝ ነበር።
በወቅቱ ጌጣ ጌጦቹን የምትሰራቸው ከጫማ ቤት በተገኘ የተረፈ ምርት እንደነበር ትናገራለች።
የእየሩሳሌም ውጣ ውረዶች
እየሩሳሌም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት እና ለመማር ባለመቻሏ ጽዳት ከመሥራት ጀምሮ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች።
ዩኒቨርስቲ ከገባች በኋላም በቀንና በማታው የትምህርት ክፍል በመማር ሁለት ዲግሪዎችን ሠርታለች።
እነዚህን ዲግሪዎች ስትሰራ ግን የትምህርት ወጪዋን ትሸፍን የነበረው እየሰራች ትሸጣቸው በነበሩት ጌጣጌጦች ነው።
የኮሌጅ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርታ እንደነበር የምትናገረው እየሩሳሌም፣ ከዚያም ሊሉያንን በመመስረት የእደጥበብ ውጤቶችን የዕለት ተዕለት ሥራዋ እና ቋሚ ገቢ የምትገኝበት ዘርፍ አደረገችው።
ሊሉያን በግዕዝ ልዩ ሕዝብ ማለት ነው።
እየሩሳሌም አፍሪካውያኖች ልዩ ሕዝቦች ነን ስትል ትገልጻለች።
ከሌላ ዓለም የምንቀዳው ነገር በጣም አነስተኛ ነው የምትለው እየሩሳሌም፤ የራስን መልክ፣ የራስን ውበት፣ የራስን ማንነት ለማጉላት ደግሞ ያልተነካ እምቅ ሃብት በአፍሪካ መኖሩን ትናገራለች።
እየሩሳሌም የምትሰራቸው ጌጣጌጦች የአንገት ሐብሎች፣ ቀለበቶች፣ የጆሮ ጌጦች እና አምባሮች ናቸው።
የኪስ ቦርሳ እና ሰነዶችን ለመያዝ የሚያገለግሉ ቦርሳዎችን ደግሞ በእጅ ከተሰፉ የቆዳ ምርቶች ትሰራለች።
ለጌጣጌጥ ምርት የሚሆኑ ግብዓቶች ከየት ታገኛለች?
እየሩሳሌም ለመጀመሪያ ጌዜ የሰራቻቸው ጌጣጌጦች ከነሐስ የተመረቱ ነበሩ።
ነሐሱን ደግሞ ከ ጥይት ቀለሃ ማግኘቷን ታስታውሳለች።
ከቀለሃ ባሻገር ደግሞ ሌሎች ነሐስ ያለባቸው እና የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ቁሶችን ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል ትሰራ እንደነበር ተናግራለች።
እነዚያን የነሐስ ምርቶች ለማስዋብ የተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች፣ አዝዕርቶችን እና ፍራፍሬዎችን እንደምትጠቀም ትናገራለች።
የጥይት ቀለሃ የምታገኘው ከአዲስ አበባ ውጪ ከክፍለሃገር መሆኑን የምትናገረው እየሩሳሌም ቀንዓ፣ ያገለገሉ የነሐስ ምርቶችን ግን ከመርካቶ ምን አለሽ ተራ ትገዛለች።
ወደዚህ ስራ እንደተሰማራች የነሐስ ምርቶችን ከተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ታገኝ እንደነበር የምታስታውሰው እየሩሳሌም፣ ነገር ግን እነዚህን ተረፈ ምርቶች ቀጥቅጦ እና አቅልጦ ወደ ጌጣጌጥ መለወጥ ለእርሷ ፈታኝ በመሆኑ ሌላ አጋሮችን በመፍጠር ከእነርሱ ያለቀለት ምርት መረከብ ጀምራለች።
ለእርሷ ግብዓት የሚያቀርቡት ሰዎች የሚገኙት አማራ ክልል ብቸና መሆኑን የምትናገረው እየሩሳሌም፣ተረፈ ምርቶቹ ቀልጠው እዚያ ጥሬ እቃዎቹ ወደ ጨሌነት ተቀይረው እርሷ ጋር እንደሚደርሱ ታስረዳለች።
እየሩሳሌም የምትሰራቸው አብዛኛዎቹ ምርቶች አፍሪካዊ ይዘት ያላቸው ጌጣጌጦች ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያዊ አሻራ እንደምታሳርፍባቸው ትናገራለች።
ጌጣጌጦቹ አፍሪካዊ አሻራ እነዲኖራቸው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ የከበሩ ድንጋዮች እና ጨሌዎችንም በስራዎቿ ውስጥ ታካትታለች።
ሊሉያን ቀጥሮ የሚያሰራቸው ልጆቻቸውን ለብቻቸው ሆነው የሚያሳድጉ እናቶችን መሆኑን እየሩሳሌም ትናገራለች።
ራሷን ጨምሮ አምስት ሴቶችንም ቀጥራ እንደምታሰራ ጨምራ ገልጻለች።
እናቶቹ ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት በዚያው ቤት ስልጠናውን እንዲያገኙ በማድረግ የምትፈልጋቸውን ምርቶች በማምረት ለእርሷ ያስረክባሉ።
በተረፈ ምርቶቿን በተለያዩ የገበያ አውደ ርዕዮች ላይ እንዲሁም ማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም ትሸጣለች።
በቅርቡ የሯሷን ድረገጽ በመክፈት ምርቶቿን በዚያ ለመሸጥ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ተናግራለች።
በምርቶቿ አፍሪካዊነትን ለበርካቶች ማስተዋወቅ ህልም የምትፈልገው እየሩሳሌም፣ ሉሊያን ወደ ፊት በገንዘብ ደርጅቶ፣ በርካታ እናቶችን በተለይ ደግሞ ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ትተው መሄድ የማይችሉትን በማሳተፍ ማደግ ትፈልጋለች።
ምርቶቿም አካባቢን የማይጎዱ እና ዘላቂ ሆነው እንደሚቀጥሉ ታስረዳለች።