በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ተቋሙ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ በትናትናው ዕለት ለ7 ሺህ 676 የላብራቶሩ ምርመራ ተደርጎ 985 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን አስፍሯል፥
በዚሁ ዕለትም በአንድ ቀን 10 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ 19 ግለሰቦች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገቡ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ በፅኑ ህሙማን ክፍል ያሉ ግለሰቦችን ቁጥር 448 ያደርሰዋል።
ተቋሙ ከሳምንታት በፊት ሶስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየጀመረ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ አስታውቋል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት መረጃዎች እና ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ታውቋል።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የኮቪድ-19 ዴልታ ቫይረስ ሲሆን በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የዴልታ ቫይረስ መኖሩ ባይረጋገጥም የሶስተኛ ዙር ወረርሽኝ መከሰቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር ካበቃ በኋላ በተወሰነ መልኩ በማህበረሰቡ መዘናጋቶች እንዲሁም የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች በአግባቡ ባለመተግበራቸው ሶስተኛው ዙር ሊከሰት የሚችልበት ምልክቶች እየታዩ ነው።
ተቋሙ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎቹ እንዲከበሩና ማስክ ማድረግ፣የእጅን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እና ርቀትን በመጠበቅ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የኮቪድ-19 መከላከከልና መቆጣጠር እንደሚቻልም አሳሳስቧል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 291 ሺህ 216 ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 266 ሺህ 80ግለሰቦች ከኮቪድ-19 ቫይረስ አገግመዋል እንዲሁም 4ሺህ 505 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። አጠቃላይ ክትባት የተከተቡ ሰዎች ቁጥርም 2,332 ሺህ 368 ነው።
አገሪቷ በአጠቃላይ 3,134 ሺህ 967 ምርመራዎችን አካሂዳለች።












