ከቤት መባረርን የሚቃወሙት የአሜሪካ የምክር ቤት አባል አንድ ሌሊት ውጭ አሳለፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምክር ቤት አባል የሆኑት ኮሪ ቡሽ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ቤት ኪራይም ባይከፈል ከቤት ማባረረን አግዶ የነበረው መመሪያ ጊዜው ማለቁን ተከትሎ ይህንን ለመቃወም በአሜሪካ ካፒቶል ደረጃዎች ላይ አንድ ሌሊት አሳልፈዋል
የዲሞክራቷ ምክር ቤት አባል ቅዳሜ የሚጠናቀቀው መመሪያ ጋር በተያያዘ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ባልተከፈለ የቤት ኪራይ ምክንያት "ከቤት የመባረር አደጋ ተጋርጦባቸዋል" ብለዋል።
በመጠለያዎች መጨናነቅ ምክንያትና የኮቪድ ስርጭትን ለማስቆም ከ 11 ወራት በፊት የማባረር እገዳው ተጥሏል።
በአንድ ወቅት ቤት አልባ የነበሩት ቡሽ እገዳው እንዲራዘም ይፈልጋሉ።
ቅዳሜ ጠዋት በትዊተር ገፃቸው ላይ "ደህና አደራችሁ። የማባረርን የሚያስቀረው እገዳ ዛሬ ማታ እኩለ ሌሊት ላይ ያበቃል። ትናንት ማራዘም ብንችልም አንዳንድ ዴሞክራቶች ግን በምትኩ ለእረፍት ሄደዋል" ሲሉ ጽፈዋል።
"ተመልሰው እንዲመጡ እና ሥራቸውን እንዲሠሩ ለመጠየቅ ትናንት ማታ በካፒቶል ተኝተናል። ዛሬ የመጨረሻ ዕድላቸው ነው። እኛ አሁንም እዚህ ነን።"
በዴሞክራቲክ ፓርቲ በበላይነት የተያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እገዳው ሳይታደስ ዓርብ ለሰባት ሳምንት እረፍት ወጥቷል።
እገዳው እንዳይራዘም የሚቃወሙት በበኩላቸው ብዙ የቤት አከራዮች ያለ መደበኛ የቤት ኪራይ ገንዘብ ለቤት ከሚከፍሉት ከብድር ክፍያቸው ጋር እየታገሉ ነው ይላሉ።
የ 45 ዓመቷ ቡሽ ወንበር ላይ የአንድ ሰዓት እንቅልፍ ብቻ ቢያሳልፉም አሁን ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ካፒቶል ደጅ ሌላ ምሽት ለማሳለፍ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቅዳሜ ዴሞክራቲክ ሴናተተሯ ኤልዛቤት ዋረን እና ሪፓብሊካኑ ጂም ማክጎቨርን ሙሉ ድጋፋቸውን ለማሰየት ቡሽን ለአጭር ጊዜ ተቀላቅለዋል።












