ታሊባን በርካታ ግዛቶችን መቆጣጠሩን ተከትሎ የሰዓት እላፊ ታወጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታሊባን ታጣቂዎች በርካታ ግዛቶችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የአፍጋኒስታን መንግሥት የሰዓት እላፊ አውጇል።
የአፍጋኒስታን መንግሥት ይህንን የሰዓት እላፊ ያወጀውም የታሊባን ታጣቂዎች ሌሎች ከተሞችን ከመውረር ለማስቆም ነው ብሏል።
ከመዲናዋ ካቡልና ሌሎች ሁለት ግዛቶች ውጭ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ሌሊት 10 ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ አይችልም።
በባለፉት ሁለት ወራት በታሊባንና በአፍጋኒስታን የመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያው ተባብሷል።
በቅርብ ሳምንት ዓለም አቀፍ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።
ታሊባን ከአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ እስከ ግማሽ ያህሉን እንደተቆጣጠረ ይገመታል።
በተለይም የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የድንበር መሸጋገሪያዎችንና በርካታ ገጠራማ ቦታዎችን መቆጣጠራቸው ተገልጿል።
ከ 20 ዓመታት ገደማ በፊት በአሜሪካ ወረራ ከስልጣን ተገፍተው የወጡት ታሊባን እንዲሁ የአቅርቦት መንገዶችን ለመቁረጥ በመፈለግ ቁልፍ ጎዳናዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል ተብሏል።
የታሊባን ተዋጊዎች ወደ በርካታ ቁልፍ ከተሞች የሚሄዱ መንገዶችን ቢዘጉም እስካሁን ዋና ዋና ከተሞችን መቆጣጠር አልቻሉም።
ካቡል ፣ ፓንጅሺር እና ናንጋርሃር ነፃ መሆናቸውን በመግለፅ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ "አመፅን ለመግታት እና የታሊባንን እንቅስቃሴ ለመገደብ በ 31 ግዛቶች የሰዓት እላፊ አዋጅ ተጥሏል" ብለዋል።
ታሊባን ወደፊት እየገሰገሰ ባለበት በዚህ ሳምንት በካንዳሃር ከተማ ዳርቻ ላይ ከባድ ወጊያዎች ተካሂደዋል።
በምላሹ የአሜሪካ መንግሥት ታሊባን በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ላይ በያዝነው ሳምንት ሃሙስ የአየር ጥቃት መፈፀሙን አስታውቋል።
ነገር ግን አሜሪካ በአፍጋኒስታን ውስጥ ታደርገው የነበረው ዘመቻ ይፋዊ በሆነ ሁኔታ በአውሮፓውያኑ ነሐሴ መጨረሻ የሚጠናቀቅ ቢሆንም በመጪዎቹ ወራቶች ምን ሊከሰት ይችላል በሚለው ሁኔታ ላይ ስጋቶች አሉ ተብሏል።












