ቱኒዝያዊው በቴኳንዶ ውድድር ለአፍሪካ የመጀመሪያዋን ሜዳልያ አስገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያዊውን በቴኳንዶ ያሸነፈው ቱኒዝያዊ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆኗል።
የቱኒዚያው መሃመድ ካሊል ጄንዱቢ ቅዳሜ ዕለት በወንዶች የቴኳንዶ 58 ኪግ ምድብ ያገኘው የብር ሜዳሊያ የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ የመጀመሪያው አፍሪካዊ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ጄንዱቢ በምድቡ ውርቁን ካጠለቀው የጣሊያኑን ቪቶ ዴላኩዊላን በመከተል ነው የብር ሜዳሊያ ለማግኘት የቻለው፡፡
ውድድሩ መጨረሻዎቹ 15 ሰከንዶች እስኪቀሩ ድረስ 10-10 በሆነ ውጤት የተጓዙ ሲሆን ባለቀ ሰዓት ግን ጣሊያናዊው ወሳኙን ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል።
የ 19 ዓመቱ ጄንዱቢ በሩብ ፍጻሜው በ 23 ነጥብ ልዩነት ኢትዮጵያዊውን ሰለሞን ቱፋ ማሸነፍ ችሎ ነበር።
ከሁለቱ የነሐስ ሜዳሊያ አንዱን የወሰደውን የደቡብ ኮሪያውን ጃንግ ጁን በማሸነፍም ድሉን ማስቀጠል ችሎ ነበር፡፡
ጄንዱቢ ሁለት ብርን ካሸነፈው ከረዥም ርቀት ሯጩ መሐመድ ጋሙዲ በኋላ የብር ሜዳሊያ ያሸነፈ ሁለተኛው ቱኒዚያዊ ለመሆን በቅቷል።
ጋሙዲ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ በተመሳሳይ ቶክዮ ላይ በአውሮፓውያኑ 1964 ነበር ያሸነፈው። ቱኒዝያ እስካሁን 14 ሜዳሊያ በኦሎምፒክ ውድድር ማግኘት ችላለች።
በሪዮ 2016 ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ቱኒዝያ በቀሪው ቶኪዮ 2020 ሌሎች ድሎችን ለማስመዝገብ በጉጉት ትጠብቃለች።












