ቤኒሻንጉል መተከል ውስጥ ሐዘን በተቀመጡ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት ደረሰ

የቤንሻንጉል ክልልን የሚያሳይ ካርታ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ አንድ ሰው ሲገደል እንዲሁም ሐዘን በተቀመጡ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት አራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።

ሐሙስ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም አንድ የከተማው ወጣት በተለምዶ ካማሺ መውጫ ወይም ማንጂ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አካባቢውን በመጠበቅ ላይ ሳለ በጥይት ተመትቶ መሞቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች እንዲሁም በቡለን ከተማ ቀበሌ አንድ እና ሁለት ካሉ ነዋሪዎች ተውጣጥተው የከተማውን ሰላም በየተራ በሚጠብቁበት አካባቢ እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ገልጸዋል።

በእዚህ ጥበቃ ላይ የነበረው ሟች ነው ማንነታቸው ባልታወቁ በሽፍታዎች ተመቶ እንደተገደለና ወደ ቡለን ሆስፒታል አስከሬኑ በአምቡላንስ መወሰዱን አመልክተዋል።

በዚህ ጊዜም "አስከሬኑ ከሆስፒታል ሲወጣ ወጣቶች እየጮሁ ሲከተሉ ነበር፤ ስሜታዊ ነበሩ። መከላከያም በቦታው ስለነበረ ወጣቶቹን ወዲያውኑ እንዲበተኑ አድርጓል" በማለት ወጣቶቹ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጸዋል።

የቡለን ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ታከለ ገሰሰም ወጣቱ ጫካ ውስጥ በጥይት ተመትቶ አስከሬኑ ወደ ሆስፒታሉ መጥቶ እንደነበር አረጋግጠዋል።

ዶክተር ታከለ አክለውም ሐሙስ ከሰዓት በኋላ አራት ሰዎችም በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን እና ሦስቱ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ባሕር ዳር መላካቸውንና አንደኛው ተጎጂ ግን አሁንም በሆስፒታሉ ተኝተው እየታከሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ቢቢሲ አቶ አዳሙ የተሰኙትን እና በቡለን ሆሰፒታል የሚገኙትን ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰብ በስልክ አግኝቶ አነጋገሯል። የ65 ዓመት አዛውንት የሆኑት አቶ አዳሙ በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰ ይናገራሉ።

በወጣቱ መገደል ምክንያት አቶ አዳሙን ጨምሮ ለሐዘን የተቀመጡ ሰዎች ላይ የኮማንድ ፖስቱ አባላት የሆኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተኩሰዋል ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆናቸውን በልብሳቸው ነው የምናውቀው። ከእኛ ጋር አብረው ስለሚኖሩ እናውቃቸዋለን። በተቀመጥንበት ነው የተኮሱብን" ብለዋል።

በለቅሶ ቤት የነበሩት ሰዎችም በተኩሱ ምክንያት መበታተናቸውን እና ቀብሩም አርብ መፈጸሙን ተናግረዋል። እርሳቸውም በቡለን ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ እንደሆነ ገልጸዋል።

የቡለን ወረዳ የኮማንድ ፖስቱ አመራር የሆኑት ሻለቃ ሰለሞን "እኛ በሕዝብ ላይ የምንተኩስ ሳንሆን ለሕዝብ ከለላ የምንሆን ነን" ሲሉ ጥቃቱ በሠራዊቱ አለመፈጸሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በወቅቱ ግርግር ስለነበረ ጥቃቱ የተፈጸመው እርስ በእርስ ሊሆን ይችላል፤ በማጣራት የሚታወቅ ይሆናል። መከላከያ ሰውን አይመታም። እስካሁንም እየጠበቅናቸው ነው። ይሄ ሌላ ከበስተጀርባው የራሱ አጀንዳ ያለው ሰው የመከላከያን ስም ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ነው" ሲሉ ሻለቃ ሰለሞን ክሱን አስተባብለዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተገድለዋል።

ከቀናት በፊትም ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል።

በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለመቆጣጠር በፌደራል መንግሥቱና በክልሉ መንግሥት የጸጥታ አካላት ጥምረት በተቋቋመ ኮማንድ ፖስት ስር ይገኛሉ።