በኢራን የውሃ እጥረት ተቃውሞ ሰልፍ አንድ ሰው ተገደለ

በደቡብ ምዕራብ ኢራን የተከሰተው ከባድ የውሃ እጥረት ተከትሎ ለሁለተኛ ቀን በ ቀጠለው ተቃውሞ አንድ ሰው መገደሉን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

በኩዝስታን ግዛት የሚገኙ አንድ ባለስልጣን እንደተናገሩት ሰልፈኛው በአጋጣሚ በአየር ላይ በሚተኩሱ ሰዎች መመታቱን የዘገበው የመንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ኢርና ነው፡፡

ተቃዋሚዎች በበኩላቸው በጸጥታ ኃይሎች ምክንያት ሞቷል ሲሉ ከሰዋል፡፡

ኢራን ከባድ ድርቅ ያጋጠማት ሲሆን የውሃ እና የኃይል እጥረት መከሰቱም የህዝብ ቁጣ እየጨመረ መጥቷል ተብሏል፡፡

ግለሰቡ የሞተው በሻዴጋን ከተማ ሲሆን ምስሎቹ በማህበራዊ ድር አምባ በስፋት ተሰራጭተዋል፡፡

የከተማው ተጠባባቂ አስተዳዳሪ ኦሚድ ሳብሪፑር ለኢርና እንደገለጹት "በሰልፎቹ ላይ አመጸኞቹ ሰዎችን ለማስቆጣት ወደ አየር መተኮስ የጀመሩ ሲሆን በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ጥይት እዚያ የተገኘውን ሰው በመምታት ገድሎታል"ብለዋል፡፡

ግለሰቡ ከኢራቅ ጋር ድንበር ላይ በሚገኘው በኩዝስታን የሚገኙት አረብ የጎሳ አባል እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከሀገር ውጭ የሚገኙ የተቃዋሚ መገናኛ ብዙሃን በሰላማዊ ሰልፎቹ ላይ በጸጥታ ኃይሎች በተከፈተ ተኩስ መገደሉን የሚገልጹት ዘገባዎች ሰርተዋል፡፡

የኢራን ባለሥልጣናት በነዳጅ በበለጸጉ በርካታ ከተሞች የተካሄዱትን የተቃውሞ ሰልፎች መጠን ዝቅ አድርገው አቅርበዋል፡፡

በድረ ገጽ የተሰራጩ እና ከሰልፎቹ የተገኙ ቪዲዮዎች እንደሆኑ በተነገረላቸው ምስሎች ላይሰዎች መንገዶችን ለመዝጋት ጎማዎች ሲያቃጥሉ ታይቷል፡፡

በአንዱ ቪዲዮ የጸጥታ ኃይሎች የአድማ ብተና ልብስ ለብሰው ህዝቡን ሲከተሉ ታይተዋል፡፡

የተቃውሞ ሰልፈኞቹን ቅሬታ ለመፍታት አርብ ዕለት የኢራን መንግስት ልዑካን ወደ አካባቢዎቹ ልኳል፡፡

የውሃ ችግሩ በግብርና እና በእንስሳት እርባታ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ ለኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ በርካታ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል ፡፡

ባለሥልጣኖቹ ለተፈጠረው ሁኔታ የዝናብ መቀነስን ይወቅሳሉ። ብዙ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች የማይሠሩ ሲሆን ሰዎችም ከፍተኛው የበጋ ሙቀት ለመቋቋም የአየር ማቀዝቀዣን ስለሚጠቀሙ የኤሌክትሪክ ፍጆታው ጨምሯል ተብሏል፡፡

የአከባቢዎቹ ነዋሪዎች ግን ችግሩ የመልካም አስተዳደር እና የሙስና ነው ይላሉ፡፡

የኢራን ኢኮኖሚ በአሜሪካ ማዕቀቦች እና በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት ተሽመድምዷል፡፡ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በኢራን የነዳጅ ኢንዱስትሪ የሚሠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች የተሻለ ደመወዝ እና የሥራ ሁኔታ በመጠየቅ አድማ ላይ ነበሩ፡፡