ታዳጊዋ የአሜሪካ 'ስፔሊንግ ቢ' በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ድንቅ የቅርጫት ኳስ ችሎታ ያላት ታዳጊ የአሜሪካን ብሔራዊ 'ስፔሊንግ ቢ' ያሸነፈነች የመጀመሪያው አፍሪካ-አሜሪካዊ ሆናለች።
ስፔሊንግ ቢ ተወዳዳሪዎች የሚነገራቸውን ቃላት ትክክለኛ ፊደላት እየተናገሩ የሚፎካከሩበት መድረክ ነው።
የሉዊዚያና ኒው ኦርሊያንስ ነዋሪ የሆነችው የ14 ዓመቷ ዛይላ አቫንት-ጋርድ “ሙራያ” (murraya) የሚለው ቃል ትክለኛ ፊደላት ተናግራ ነው ያሸነፈችው። ሙራያ በሞቃታማ አካባቢ የሚገኝ የዛፍ ዓይነት ነው።
ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ “querimonious” እና “solidungulate” የተሰኙትን ቃላት ፊደላት በትክክል መናገር ነበረባት።
ምንም እንኳን በቀን እስከ ሰባት ሰዓታት ያህል ብትለማመድም የቃለት ፊደልን መናገርን የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ አድርጋ ነው የምትመለከተው። ዛይላ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ለመሆን ነው ፍላጎቷ።
በአንድ ጊዜ በርካታ ኳሶችን በማንጠር ሦስት የዓለም ክብረወሰኖችን ስትይዝ ከናሽናል ባስኬትቦል አሶስዬሽን (ኤንቢኤ) ኮከቡ ስቴፈን ከሪ ጋር ማስታወቂያ የመሥራት እድልም አግኝታለች።
ዛይላ ሐሙስ ዕለት ከአስራ አንድ የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች ጋር ተፎካክራ አሸናፊ ሆናለች። በፍሎሪዳ ኦርላንዶ የተካሄደውን ዝግጅት በማሸነፏም 50,000 ዶላር አግኝታለች።
በመጨረሻው ዙር የፍሪስኮ ቴክሳስዋን ነዋሪ እና የ 12 ዓመቷን ቻይትራ ቱማላን አሸንፋለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እአአ ከ 2008 ወዲህ የእስያ ዝርያ የሌለው/የሌላት አሸናፊ ወይም ከአሸናፊዎቹ መካከል አንዱ/ዷ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለድል ሳይሆኑ የቀሩበት መድረክ መሆኑን አሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ዛይላ በፍጻሜው ቀን ‘ኔፓታ’ (የሚንት ዝርያ ነው) በሚለው ቃል ላይ ያመነታች ቢሆንም በትክክል ፊደሉን መጥራት ችላለች፡፡
በቤት ውስጥ የምትማረው ታዳጊ ለኒው ኦርሊያንስ ጋዜጣ ታይምስ-ፒካዩን “አብዛኛውን ጊዜ ወደ 13,000 ቃላት [በየቀኑ] ለማጥናት እሞክራለሁ። ይህ ደግሞ እስከ ሰባት ሰዓት ወይም ተቀራራቢ ጊዜ ይወስዳል” ብላለች።
“በእርግጥ ከመጠን በላይ በሆነ መንገድ እንዲሄድ አንፈቅድም። ትምህርት እና ቅርጫት ኳስም አለብኝ።“
ዛይላ ውድድሩን ያሸነፈች ሁለተኛዋ ጥቁር ታዳጊ ሆናለች። የጃማይካዋ ተወላጅ ጆዲ አን ማክስዌል እአአ በ1998 በ12 ዓመቷ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡
በ2019 ስምንት ሕጻናት በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩ ባለፈው ዓመት ተቋርጦ ነበር።












