የትግራይ ኃይሎች ከመቀለ አልፎ ሌሎች ከተሞችንም እየተቆጣጠሩ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትግራይ አማፂያን የክልሉ ዋና ከተማ መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሌሎች ከተሞችንም መያዝ መጀመራቸው ተገለጸ።
የፌደራሉ መንግሥት መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ከቀናት በፊት የትግራይ መዲና መቀለን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።
አማፂያኑ በሰሜን ምዕራብ የምትገኘው የሽረ ከተማን እንደተቆጣጠሩ የተባበሩት መንግሥት ሠራተኞች አስታውቀዋል።
ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በበኩሉ አማፂያኑ በአሁኑ ወቅት የክልሉን አብላጫ ክፍል መቆጣጠራቸውን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ሲያግዙ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች ቀደም ብሎ ከተማዋን ለቀው መውጣታቸው ተዝግቧል።
ምንም እንኳ መንግሥት ጦርነቱ ስምንት ወራት ካስቆጠረ በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጊያለሁ ቢልም አማፂያኑ ግን "ጠላትን" ያሉትን ኃይል ከትግራይ ለማስወጣት ዝተዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሰኔ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም በተናጠል ያደረገው በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት እንዲቆም በሚል ነው።
በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በመንግሥት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል።
ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ሲፈናቀሉ 350 ሺህ ገደማ ደግሞ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል።
ግጭቱ ባለፈው ኅዳር የተጀመረ ሲሆን የመንግሥትን የለውጥ ሂደት የተቃወሙት አማፂያኑ የመከላከያ ሠራዊቱን መቀመጫ በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ነበር።
መንግሥት የክልሉ መናገሻ መቀለን የተቆጣጠረው ከግጭቱ መጀመር ከሳምንታት በኋላ ነው።
አማፂያኑ ማክሰኞ ዕለት ወደ ዋና ከተማዋ መቀለ ሲገቡ ሰዎች በደስታ ሲቀበሏቸው ታይቷል።
ማዕከላዊው መንግሥት የተኩስ አቁም ማወጁን ይፋ ባደረገበት መግለጫ "የሰብዓዊ እርዳታ ተኩስ አቁም" እንዲደረግ አውጇል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ለሮይተርስ የዜና ወኪል የትግራይ ኃይሎች ወደ ኤርትራም ሆነ ወደ አማራ ክልል ገብተው "ጠላትን ሊያጠፉ" ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።
"ጠላት የሕዝባችንን ደኅንነት መልሶ አደጋ ላይ መጣል እንደማይችል እርግጠኛ መሆን አለብን" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በትግራይ ክልል ያሉ የኤርትራ ወታደሮች ሁኔታ አሁንም ግልፅ አይደለም፤ ነገር ግን አንድ የሽረ ነዋሪ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ድንበር አካባቢ ሲሄዱ አይቻለሁ ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።
በትግራይ ክልል ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም አካላት የጅምላ ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው ይከሰሳሉ።
ባለፈው ማክሰኞ አንድ ነባር የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን አሜሪካ "በትግራይ ክልል እየተፈፀመ ያለውን ጥሰት እያየች ዝም አትልም" ብለዋል ነበር።
የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ "የተኩስ አቁም እወጃው ወደ ጦርነቱ ማብቃት፣ ጭካኔ ማቆምና የሰብዓዊ እርዳታ መዳረስ የሚወስድ ከሆነ በጣም መልካም ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ክልል የረሃብ አደጋ አለ ቢልም መንግሥት ግን ይህንን ያስተባብላል።













