አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ አማራ ልንዘምት እንችላለን ሲሉ የክልሉ ብልጽግና ጽ/ቤት በበኩሉ የህወሓት ኃይሎችን አልታገስም አለ

የትግራይ ኃይሎች

የህወሓት ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ወደ አማራ እና ኤርትራ ልንዘምት እንችላለን ሲሉ የአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት በበኩሉ የህወሓት ኃይሎችን አልታገስም አለ።

የፌደራሉ መንግሥት ሰኔ 21 2013 ዓ.ም የመቀለ ከተማን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ አማፂያን የክልሉ ዋና መዲና ከተቆጣጠሩ በኋላ ሌሎች ከተሞችንም መያዝ መጀመራቸው ተገልጿል።

የትግራይ ኃይሎች መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ወደ አማራ ክልል መሄድ ካለብን እንሄዳለን፤ ወደ ኤርትራ መዝመት ካለብን እናደርገዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ጌታቸው ረዳ "ዋና ዓላማችን የጠላትን የመዋጋት አቅም ማዳከም ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ከኤርትራ፣ ከአማራ ወይም ከአዲስ አበባ በኩል ያሉ ጠላቶች የሕዝባችን የደህንነት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን" ብለዋል።

የፌደራሉ መንግሥት መቀለን ለቅቆ ወጥቶ ግጭቱ እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚል ምክንያት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ ኃይሎች በርካታ የክልሉን ስፍራዎች እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙ ተዘግቧል።

አማፂያኑ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የምትገኘው የሽረ ከተማን እንደተቆጣጠሩ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች አስታውቀዋል።

ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በበኩሉ አማፂያኑ በአሁኑ ወቅት የክልሉን አብላጫ ክፍል መቆጣጠራቸውን አስታውቋል።

"የህወሓት ኃይሎችን በዝምታ ታገስም"

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት በበኩሉ የህወሓት አመራሮች "በተደጋጋሚ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት የአማራን ልሂቃንን ተጠያቂ በማድረግ ሂሳብ እንደሚያወራርዱ ነግረውናል" ብሏል።

የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የህወሓት አመራሮች "የሚያወራርዱትን ሂሳብ" ከአማራ ልሂቃን ጋር ያያይዙት እንጂ እውነታው ግን የአማራ ሕዝብ ስለማለታቸው ጥርጣሬ እንደሌለው ገልጿል።

"የአማራ ሕዝብ በትህነግ ዳግም ሊሰነዘርበት የታሰበውን የጥፋት ሰይፍ በደንብ ተረድቶታል። የብሔራዊ ንቃት ስሜቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል" ያለው ፓርቲው፤ "በፍቅር ለመጣ በተለመደ ሰብዓዊ ጀግንነቱ እጁን ይዘረጋል፤ በጥላቻ ለሚመጣ ተገቢውንና የማያዳግም ትምህርት ሰጥቶ ይመልሳል" ብሏል።

" ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋዕትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን " ሲል ፓርቲው ጨምሮ አሳስቧል።

ጽ/ቤቱ እነዚህን አካባቢዎች ደግሞ ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ፣ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌለ መሆኑን ደግመን ደጋግመን እናረጋግጥላችኋለን።" ብሏል በመግለጫው።

ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች የክልሉን መዲና መቀለን መቆጣጠራቸውን ሲያሳውቁ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል የተናጥል ተኩስ አቁም አውጇል።

ይህንንም ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሰንደቅ አላማ በማውለብለብና ርችት በመተኮስ ደስታቸውን ሲገልፁ እንደነበር ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።

በትግራእ ክልል ላለፉት ስምንት ወራት የተካሄደው ጦርነት ክልሉን ከፍተኛ ወደ ሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ከትቶታል።

በክልሉ አምስት ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰረት 350 ሺህ ሕዝብ የሚሆነው በረሃብ ቋፍ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ክልሉን ያስተዳድር የነበረውን ህወሓት ከስልጣን ለማስወገድ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ህወሓት ግንኙነታቸው በዋነኝነት የሻከረው በአገሪቱ ላይ ባሉ ፖለቲካዊ ለውጦች በተለይም ብሔርን መሰረት ባደረገው የፌደራል ሥርዓት ጋር በተገናኘ ነው።

ህወሓት የሰሜን ዕዝ መቆጣጠሩን ተከትሎ ጦርነቱን አቀጣጣጥሎታል ተብሏል።

በክልሉ ውስጥ በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላት የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ይወነጀላሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችም ተገድለዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, 'ልጄ የሞተበትን ስፍራ ላለማት ስል ቤተክርስትያን መሄድ ተውኩኝ።'