ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጦሩ ከመቀለ የወጣው ተሸንፎ አይደለም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Prime Minister office screen grab
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፌደራል መንግሥት ወታደሮቹን ከመቀለ ያስወጣው ተሸንፎ አይደለም አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ትናንት ሰኔ 22/2013 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ ነው።
የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ወታደሮቹን ማስወጣቱንና የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች መቀለን ጨምሮ አንዳንድ ከተሞችን መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግር "ጦሩ የወጣው በሽንፈት ሳይሆን ኦፕሬሽኑ (ዘመቻው) በመሳካቱ ነው" ብለዋል።
"አሁን የተካሄደው ኦፕሬሽን (ዘመቻ) ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተሳክቷል፤ የምንፈልገውን ሠራዊታችንን አስወጥተናል። ይህም ሌሎች ኃይሎች የሚያስቡት ነገር ካለ ለመዘጋጀት ሰፊ ዕድል አግኝተንበታል" ሲሉ ተናግረዋል።
ህወሓት በበኩሉ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ የትግራይ ክልል አስተዳደር ሲል ባወጣው መግለጫ "አስደናቂ ድል ተገኝቷል፤ መቀለም በትግራይ መከላከያ ኃይል በሙሉ ቁጥጥር ስር ናት" ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው "የጁንታው ኃይል መቀለ አልደረሰም፤ ህወሓት ሳይሆን መቀለ የገባው በአካባቢው የነበረ፣ ጠመንጃውን የደበቀና ጊዜ የሚጠብቅ ኃይል ነው" ብለዋል።
"እኛ ስንዴ እየሰጠን፤ እኛ ዞር ስንል የሚጨፍር ከሆነ የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል ማለት ነው" ሲሉ ለሕዝቡ ጊዜ መስጠት በማስፈለጉ ውሳኔ ላይ መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በመቀለ ያለው ጦር ብዛት 20 ሺህ ያህል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጦሩ ከትግራይ ክልል ሲወጣ የጦር መሳሪያ ማስወጣቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ውስጥ ሠራዊቱ ለምን እንደገባና በአሁኑ ወቅትም ለምን እንደወጣ በዚሁ ወቅት አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊታቸው ወደ ትግራይ ከዘመተ በኋላ የመቆየት አላማ እንዳልነበረው ተናግረው፤ "ሌላ የሚያሰጋን ኃይል ስላለ ወደእሱ መዞር ያስፈልገን ነበር፤ ይህ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው" ብለዋል።
ይህ ያሰጋል ያሉት ኃይል ግን ማን እንደሆነ በዚህ ወቅት አልጠቀሱም።
በተለይም ባለፉት ሳምንታት ጦርነቱ አቅጣጫውን እንደቀየረ በተናገሩበት በዚህ መግለጫ፤ የክልሉ ሕዝብ በጦርነቱ ተሳትፏል ብለዋል።
"አሁን ያለው ጦርነት ይለያል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ባለፉት 20 ቀናት "ሕዝቡ ራሱ ወታደሩን ማጥቃት ጀምሯል" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "ወታደሩ ከመቀለ ባይወጣ ኖሮ የዚህ ቤት ድንጋጤ የተገለበጠ ይሆናል። ቄሶች የድምጽ ማጉያ እና ጠመንጃ ይዘው ታይታዋል፤ በመቃብር ስፍራዎች ትጥቅ ተቀብሯል" ብለዋል።
"አሁን ያለብንን ስጋት ትተን እዚያ ብንጋጋጥ ሁለቱንም ያጣ ከመሆን ያለፈ ጥቅም አይገኝበትም፤ ምክንያቱም መሰላቸት፣ መዳከም ውስጥ ገብተናል። መጀመሪያ የገጠመንን ጦር ከ15 እስከ 20 ቀን ነው የፈጀብን፤ ቀጥሎ የሽፍታ ባህርይ ያለው ተዋጊ ገጥሞን ነበር፤ እሱም ያን ያክል አልከበደንም፤ ይህ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ስለሚያስችል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ "መቀለ አሁን በወታደራዊ ዕይታ ምንም የሚያጓጓ አይደለም። ቀድሞውኑም ወታደሮቻችን ተመቱ ብለን እንጂ መቀለን ነጻ እናውጣ ብለን አልነበረም የሄድነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመቀለ ሠራዊቱ መውጣቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "አማራ ተካደ" የሚሉ ሃሳቦች መንሸራሸራቸውን አንስተው ከእውነት የራቀ ሲሉ አጣጥለውታል።
"አማራ ከትግራይ ከሱዳንና ከሌላውም ክፍል ከፍቅር ውጪ፤ በኃይል ማንበርከክ ለሚፈልገው ራሱን መከላከል የሚችል ሕዝብ ነው" ብለዋል።
ከሰሞኑ ከመቀለ ውጭ በህወሓትና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያዎች እንደነበሩ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዘገባው እንዳስነበበው ሰኞ እለት ባልተጠበቀ ሁኔታ የትግራይ ኃይሎች ክልሉን የተቆጣጠሩ ሲሆን ይህም በባለፈው ወራት የነበረው ጦርነት ሁኔታዎችን ይቀይራል ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን "ጠላት ተሸንፎ አያውቅም፤ በየቀኑ ይደመስሱናል፤ በየቀኑ ነው የምንሸነፈው በፌስቡክና በትዊተር" ሲሉ ተናግረዋል።
"የህወሓት አላማ ማሸነፍ ሳይሆን 'አመድ ሆኛለሁና ተያይዘን አመድ እንሁን፤ ተከስክሻለሁና አብረን እንከስከስ' ዓይነት አላማ ነው ያላቸው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በስምንት ወራት ውስጥ ጦርነት በተካሄደባት ትግራይ በርካታ ወታደሮች እና ሲቪሎች መገደላቸውን መንግሥት አስታውቋል። በዚሁ ወቅትም ከወታደራዊ መልክ ካለው ወጪ በተጨማሪ ለመንገድ፣ ለመብራት፣ ለትምህርትና ለጤና 100 ቢሊዮን ብር መውጣቱን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ወጪ ከክልሉ በጀት እንዲሁም ከአገሪቱ በጀትም ጋር አነጻጽረውታል።
"የወጣው ገንዘብ በዘንድሮ የሚያዘው በጀት 20 በመቶ እንዲሁም ከትግራይ ዓመታዊ በጀት 13 እጥፍ በላይ ነው" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "በመብራት ጥገና፣ በእርዳታ አቅርቦትና በሌሎች ሥራዎች ላይ እያሉ ሰዎች ተገድለዋል። ግን አንድም ሰው ጥሩ ሰራችሁ ያለን የለም፤ ክሶች ብቻ ነበር ሲቀርቡ የነበሩት" ሲሉም መገናኛ ብዙኃንን ወቅሰዋል።
"አንድም ሰው በርቱ ጥሩ ሥራ እሰየራችሁ ነው ቀጥሉ የሚልን ሰው አልገጠመንም፣ ይልቁኑም በእናንተ ምክንያት ረሃብ ሊመጣ ነው፣ ውጊያ አላቆማችሁም፣ ለኤርትራ ሠራዊት ፈቀዳችሁ ብሎም ፍቃድ ከለከላችሁ የሚል ነበር" ሲሉ ገልጸዋል።
የተለያዩ ተቋማት በበኩላቸው ጦርነቱ ክልሉን ከፍተኛ ወደ ሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ከትቶታል ይላሉ።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ በክልሉ አምስት ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን 350 ሺህ ሕዝብ የሚሆነው በረሃብ ቋፍ ላይ ነው።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ረሃብ አለ የሚለውን የተለያዩ ተቋማት መግለጫ እንደማይቀበለው ማስታወቁ ይታወሳል።
በክልሉም ረሃብ እንደሌለና እርዳታም እየተከፋፈለ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል።
በክልሉ ወስጥ ህወሓት በደርግ ወቅት እንዳደረገው በስንቅ እና ትጥቅ ራሱን ማደራጀቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ነዋሪው 'አምስት ቤተሰብ ቢኖረው 10 አለኝ' ብሎ በማስመዝገብ ግማሹን ለጁንታው ይሰጣል። ረዘም ያለ ጊዜ በፈጁ ጦርነቶች ወቅት መከላከያ ውሃ ይከላከላል፣ ጁንታው ሃይላንድ እና የስ ያገኛል" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደሩ "ጠላት" ብለው በጠሩት ኃይል ብቻ ሳይሆን የክልሉም ሕዝብ ሠራዊቱን እንዳጠቃ አስረድተዋል።
"ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ወታደሩ ሲሄድ ጠላት ሳይሆን ሕዝብ ያያል" ያሉት ዐቢይ፤ አነስተኛ ወታደር ያነሰ ሲሆን ከኋላ በርከት ያሉ ሰዎች ወረውት በክላሽም በገጀራም ይጨፈጭፉታል።" በማለት ተከላከሉልን ያሉ ሰዎችም ሠራዊቱን አጥቅተዋል በማለት ተናግረዋል።
"አንድ መንደር ላይ ጁንታው አልደገፋችሁኝም በሚል ሰዎች ይረሽናል። 'እየረሸኑን ነው ጥበቃ አታደርጉልንም' ብለው ጠየቁ ወታደሩን። በዚያ መንደር መካለከያ በቁጥር ከ20 የማበልጡ ሰዎችን አስቀምጦ ሄደ። ጠዋት ጠብቁን እንዳትሄዱብን ያሉ ሰዎች ከሰአት ወጥተው እነዚያን ወታደሮች ፈጇቸው" ብለዋል።
ይህንንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለሳምንታት ውይይት ከተረገ በኋላ ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
በተለይም ባለፉት ሦስት ሳምንታት ሕዝቡ በመሳተፉ "ሕዝብ ላይ አልተኩስም ብለው ራሳቸውን ያጠፉ አሉ፤ ጥይት ጨርሰው የተገደሉ እና የተያዙም ወታደሮች ነበሩ" ብለዋል።
"እኛ የወሰነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝብን እንደጠላት ወስዶ፣ በታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ፣ እሱም የሚሸማቀቅበት ዓለምም ኢትዮጵያ ላይ የሚነሳበት ነገር ከሚፈጠር፤ ደጀን ወደሚለው ሕዝብ ጠጋ ብለን፤ በምርጫው የጥሞና ጊዜ እንደተባለው ለሕዝቡ ይህንን የጥሞና ጊዜ እንስጠው ብለን ነው። ሳምንታትን ወይም አንድ ሁለት ወር ስንሰጠው እናየዋለን የመንግሥትን እና የመከላከያን ጥረት በብዙ እጅ መረዳት ሲጀምር።" ሲሉ ተናግረዋል።
ተመድን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በክልሉ ውስጥ በወታደሮች ንፁሃን ዜጎች እንደተጨፈጨፉ እንዲሁም ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀማቸውን ይከሳሉ።
የተመድ የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በቅርቡ ለፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ላይ "ሴቶችንና ታዳጊዎችን በተቀናጀ ሁኔታ በመድፈር ለማሸበርና ለማሰቃየት እየተጠቀሙበት ነው። የኤርትራ ወታደሮች ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው። የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ይከበባሉ፣ ይደበደባሉ እንዲሁም ማስፈራሪያዎች ይደርሳቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ የመንግሥት ተናጠል የተኩስ አቁምን ተከትሎም የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ በሰጡት መግለጫ "ትግራይ ከወራሪ ኃይሎች ነፃ እስክትሆን ድረስ" ውጊያው እንደማያቆም አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ቦታዎቹን ባይጠቅሱም ሠራዊቱ ይዟቸው የሚቆዩ ቦታዎች እንዳሉ እና ወደዚያ የሚመጣ ኃይል ካለም አስፈላጊውን ዝግጅት እንደተደረገ ጠቁመዋል።












