የቀድሞው የዛምቢያ መሪ ኬኔት ካውንዳ በ97 ዓመታቸው አረፉ

የመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዝዳንትና በአገሪቱ የነጻነት ትግል ወቅት ቁልፍ ሰው የነበሩት ኬኔት ካውንዳ በ97 ዓመት እድሜያቸው ማረፋቸውን ቤተሰባቸው አስታወቀ።

ካውንዳ ሰኞ ዕለት በሳንባ ምች ህመም ምክንያት በዋና ከተማዋ ሉሳካ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል ገብተው የነበረ ሲሆን ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ረዳቶች የካውንዳ ሞት ምክንያት ኮሮናቫይረስ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ኬኔት ካውንዳ በአውሮፓውያኑ በ1950ዎቹ የሰሜን ሮዴዢያ የነጻነት እንቅስቃሴ የተባለውና ዛምቢያን ከብሪታኒያ ነጻ ለማውታት በሚታገለው ቡድን ውስጥ ዋነኛ ሰው ነበሩ።

በ1964 (እአአ) የዛምቢያ ነጻ መውጣትን ተከትሎም ካውንዳ የአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት በመሆን ለ27 ዓመታት መርተዋታል።

ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለአስርታት ዛምቢያን የመራውን የግራ ዘመሙ የፖለቲካ ፓርቲያቸው መሪ በመሆን አገሪቱን በአንድ ፓርቲ አመራር ስር አቆይተዋታል።

ከ30 ዓመት በፊት በተካሄደውና በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ሥልጣናቸውን አስረክበዋል።

ኬኬ በመባል በስፋት የሚታወቁት ካውንዳ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የነበረው የዘር መድልኦ ሥርዓት እንዲያበቃ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ይነገራል።

በተጨማሪም በሞዛምቢክና በዚምባብዌ ይደረጉ የነበሩትን የነጻነት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ከሚጠቀሱ መሪዎች መካከል ነበሩ።

"የአባቴን ማረፍ ሳረዳችሁ በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ሆኜ ነው" ሲል ልጃቸው በአባቱ ፌስ ቡክ ገጽ ላይ የኬኔት ካውንዳን ዜና እረፍት ይፋ አድርጓል "በጸሎታችን እናስበው" ሲልም አስፍሯል።