ሳዑዲ አረቢያ አንድ ግለሰብ በታዳጊነቱ 'ፈጽሞታል ለተባለው ጥፋት' በሞት ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, REPRIEVE
የሳዑዲ አረቢያ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሰዎችን የሞት ቅጣትን አስቀርቻለሁ ብትልም አንድ ወጣት በ17 ዓመቱ ለፈፀመው ድርጊት በሞት ቀጣች።
በሞት የተቀጣው ሙስጠፋ ሀሸም አል-ዳርዊሽ የተሰኘው ወጣት ከአምሰት ዓመት በፊት ከተካሄደ ተቃውሞ ጋር በተያያዙ ጥፋቶች ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።
የሳዑዲ ባለስልጣናት የሽብር ቡድን በመመስረት እና የትጥቅ አመፅ ለማካሄድ ሞክሯል ሲሉ ነበር ክስ የመሰረቱበት።
ነገር ግን የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች የፍርድ ሂደቱ ፍትሃዊ አልነበረም በማለት የሞት ፍርዱ እንዳይፈፀም ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሪፕሪቭ የተባለ የፀረ-ሞት ቅጣት በጎ አድራጎት ድርጅት እንዳሉት የ26 ዓመቱ አል-ዳርዊሽ በቅርቡ የማሰቃየት ተግባራት ከተፈፀሙበት በኋላ የእምነት ቃሉን ሰጥቷል።
የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ግን በዚህ ላይ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።
የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የአል-ዳርዊሽ ክሶች "አመጽ በመቀስቀስ ደኅንነትን ለማወክ መፈለግ" እና "አለመግባባት በማስፋፋት" የሚሉ ይገኙበታል።
በአል-ዳርዊሽ ላይ ከቀረቡት ማስረጃዎች መካከልም "ለፀጥታ ኃይሉን ክብር የሚነካ" ምስል እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2011 እና በ2012 ከአስር በላይ "የአመጽ" ስብሰባዎች ላይ ተሳትፏል የሚሉት ይገኝበታል።
የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሰው የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት አል-ዳርዊሽ "የአካባቢውን የፀጥታ ኃይሎች ለመግደል ሙከራ አድርጓል" የሚል ክስም ይገኝበታል።
ሆኖም ግን ፍርድ ቤት የቀረቡ የትኞቹም ሰነዶች በግለሰቡ ተፈጸሙ የተባሉት ጥፋቶች አንዳቸውም ተፈፀሙ የተባሉበት ቀን አልተጠቀሰም።
ሪፕሪቭ የአል-ዳርዊሽ ቤተሰቦች ቀደም ሲል ስለ ቅጣቱ መፈፀም ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልተቀበሉ እና በኢንተርኔት ላይ ዜናውን እንደሰሙ ተናግረዋል ብሏል።
ሪፕሪቭ ይፋ ባደረገው የቤተሰቦቹ መግለጫም "እንዴት አንድ ልጅ በስልኩ ውስጥ በተገኘ ፎቶግራፍ የተነሳ ይገደላል?" ሲሉ ጠይቀዋል።
"ልጃችን ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከስቃይ ውጪ ሌላ የምናውቀው ነገር የለም፣ ይህ ለመላው ቤተሰቡ በህይወት እያለን ሞት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የመንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ኤስፒኤ የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አል ዳርዊሽ በነዳጅ በበለፀገችው የአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ዳማም ውስጥ ነው የሞት ቅጣቱ የተፈጸመበት።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት ባለፈው ዓመት ለአካለ መጠን ሳይደርሱ ወንጀል በፈጸሙ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት እንደማይተገበር እና ይልቁንም ቢበዛ የ10 ዓመት እስራት ብቻ እንደሚፈጽሙ ገልጸው ነበር።
ንጉሣዊ ድንጋጌው የአዲሱ ሕግ አፈፃፀምን ለሚጠብቁ ሰዎች ውሳኔው ወደኋላ ተመልሶ እንደሚሠራ ተገልጾ ነበር። አምነስቲ እና ሪፕሪቭም የአል-ዳርዊሽ ጉዳይ በአዲሱ ሕግ መሰረት መታየት አለበት ሲሉ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የተለያዩ የመብት ቡድኖች የዚህን የለውጥ አተገባበር በተመለከተ ስጋታቸውን ደጋግመው ሲገልፁም ሰንብተዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሳዑዲ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በሞት ፍርድ የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ሲል ገልፆ ነበር።
ሆኖም ሪፕሪቭ ይፋ እንዳደረገው ሳዑዲ አረቢያ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የፈፀመቻቸው የሞት ፍርድ ቅጣቶች ባለፈው ዓመት በሙሉ ከተገደሉ ሰዎችን ቁጥር እኩል ሆኗል።














