የቻይናው ፕሬዚዳንት አገራቸው በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ እንድትከተል ጥሪ አቀረቡ

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ አገራቸው ወዳጆቿን ማብዛት እንደምትፈልግ አስታውቀዋል።

ለዚህም አገራቸው የገፅታ ግንባታ ያስፈልጋታል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከኮሙኒስት ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራቸው "ታማኝ፣ ተወዳጅና ክብር ያላትን የቻይናን ገፅታ መፍጠር አስፈላጊ ነው ማለታቸውን የአገሪቱ የዜና ወኪል ሺኑዋ ዘግቧል።

ቻይና ከምዕራባውያኑ ጋር ያላት ግንኙነት ከአመት አመት ወደ ባላንጣነት እንደተሸጋገረ የሚናገሩት ተንታኞች ቻይና ይህንን ማለቷ መሰረታዊ በሆነ መልኩ ዲፕሎማሲያዋን ልትቀይር መሆኑ አመላካች ነው።

ቻይና በተለይም እንደ አሜሪካ ጋር ካሉ ታላላቅ ኃያላን አገራት ጋር የሻከረ ግንኙነት ነው ያላት።

በአገሪቷ ባሉ ሙስሊም ህዝቦች ላይ በምታደርሰው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በሆንግ ኮንግ የዲሞክራሲ ደጋፊዎች በምታደርሰው እስሮችና እንግልቶች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቻይና ከፍተኛ ውግዘቶችን አስተናግዳለች።

በቅርቡም አሜሪካ የኮቪድ-19 መነሻ የቻይና ቤተ ሙከራዎች ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ አደርጋለሁ ማለቷን ተከትሎ ቻይና በበኩሏ "የራሳቸውን ጥፋት ለመደበቅና ፖለቲካዊ ማጭበርበር" ነው በሚል አፀፋዊ ምላሽ ሰጥታለች።

ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ሰኞ እለት ከባለስልጣኖቻቸው ጋር በመከሩበት ወቅት ቻይና ታሪኳን በአዎንታዊ መልኩ ልትናገር ይገባል ብለዋል።

"አጋሮችና ወዳኞች ማፍራት አስፈላጊ ነው።በአለም አቀፉ ዘንድ ያለውን ዋነኛ የህዝብ አስተያየትን ለማስቀየር የወዳጆቻችንን ቁጥር መጨመር አስፈላጊ ነው" ማለታቸውንም ሺኑዋ ዘግቧል።

አክለውም አገራቸው ከአለም ጋር በምታደርገው ግንኙነት "ግልፅና በራሷ የምትተማመን እንዲሁም ራሷን ከፍ የማታደርግ" ሆና መታየት እንዳለባት አስረድተዋል።

ፖርቲው በሚሰራቸው የፕሮፖጋንዳ ስራዎችም መንግሥታቸው "ለቻይና ህዝብ ደስታና ብልፅግና የሚሰራ ነው" የሚለውን አፅንኦት መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱን ንግግር ያጤኑ ተንታኞች መሪው ለመጀመሪያ ጊዜ የቻይናን መገለልና ብቸኝነት ያመኑበት ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ የቻይና ፕሬዚዳንትነትን ስልጣን የጨበጡት በአውሮፓውያኑ 2012 ሲሆን በቁርጠኝነትና በጨቋኝነት ይተቻሉ።

በአገሪቱ ላይ ለሚሰነዘሩ ማንኛውም አይነት ተቃውሞዎች የአገሪቱ ዲፕሎማቶች ምላሽ ማጣጣል ወይም ደግሞ በጠብ አጫሪነት ነበር።