አሜሪካና ቻይና አዲስ 'ቀዝቃዛ ጦርነት' ላይ ናቸው?

ጆ ባይደንና ዢ ጂንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካን መንበረ ሥልጣን ከወራት በፊት የተረከበው የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የቻይና አቻዎቻቸው በቅርቡ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል።

በዓለም አቀፉ መድረክ የሚፎካከሩት ሁለቱ ኃያላን አገራት ግንኙነት ምን መልክ ይኖረዋል የሚለውም የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል።

ተንታኞች አገራቱ ሰላምና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ የሚፋጠጡበት ሁኔታ ይጨምራል በማለት እየተነበዩ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ከቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ይ ሃሙስ በአላስካ ይገናኛሉ።

በባይደን አስተዳደር በኩል ይኼንን ግንኙነት አስመልክቶ ምንም አይነት ብዥታ የለም ተብሏል። ከስብሰባው ቀደም ብሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን "ስትራቴጂያዊ ውይይት አይደለም" ብለው ጠንከር ያሉ ጉዳዮች የሚነሱበት እንደማይሆን ጠቆም አድርገዋል።

አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካ ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት ተጨባጭ የሆኑ ሂደቶችና ውጤቶች የሚገኙበት መሆን አለበት ብለዋል።

በዓመታት ውስጥ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው ሁለቱ አገራት ከዚህ በኋላም ቢሆን ወደ ወዳጅ ሳይሆን ወደ ባላንጣነት ያመራሉ እየተባለ ነው።

የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጄክ ሱሊቫን ከሹመታቸው በፊት ከባይደን የእስያ ጉዳዮች አማካሪ ከርት ካምቤል ጋር ፎሬይን አፌይርስ ላይ በፃፉት ፅሁፍ በድፍረት "አሜሪካ ከቻይና ጋር የሚኖራት ግንኙነት ወደ ባላንጣነት ተቃርቧል" ብለዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነትንም በተመለከተ ተንታኞች 'ቀዝቃዛው ጦርነት" ይሉት ጀምረዋል።

እንደሚታወሰው ቀዝቃዛው ጦርነት በአሜሪካና በሶቭየት ሕብረት መካከል 20ኛው ክፍለ ዘመንን ያጋመሰ፣ በትውልዶች የቀጠለ ከፍተኛ ፉክክር ነበር።

የዋሽንግተንና የቤጂንግ ግንኙነት በምን መንገድ ነው የሚታየው የሚለው ከፍተኛ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል። ምክንያቱም የሁለቱን አገራት ግንኙነት አስመልክቶ መጠየቅ የሚገባንን ጥያቄዎችና የምናገኛቸውን መልሶች ዐውድ ስለሚወስኑት ነው። የሚወጡ ፖሊሲዎችን ቀድሞ ለመጠቆምና አገራቱ ምን አይነት መንገዶችን ሊያዩ ይገባል የሚለውንም ያሳየናል።

ምንም እንኳን ታሪካዊ ትንታኔዎችን መጠቀም የአሁኑን ዐውድ፣ ውዝግብና ሁኔታዎችን ግልፅ አድርጎ ያሳያል የሚሉ ቢኖሩም፤ በተፃራሪው ታሪክ ራሱን በዚያው መንገድ ስለማይደግም የታሪክ ትንታኔዎች ልዩነትን በማጉላት የበለጠ ግንኙነትን ሊያሻክሩ ይችላሉ የሚሉም አሉ።

'ቀዝቃዛው ጦርነት' ስንል በሁለት የፖለቲካ ሥርዓታቸው የጎላና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለመጠበቅ የትኛውንም ኃይል ለመጠቀም ወደኋላ የማይሉና ትንቅንቅ የገቡ በሚል የምንረዳው ከሆነ፤ እውነት ነው የአሜሪካና የቻይና ግብግብ የአሜሪካና የሶቭየት ሕብረት ውጥረት ሌላኛው የሳንቲም ገፅታ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲና የሶቭየት ሕብረት መሪ ኒኪታ ክሩስቼቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲና የሶቭየት ሕብረት መሪ ኒኪታ ክሩስቼቭ

የባይደን አስተዳደር ጊዜያዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስትራቴጂን ስናይ፤ ቻይና ብቸኛ ተወዳዳሪዋ እንዲሁም ምጣኔ ኃብታዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊና የቴክኖሎጂ ሃይሏን በማጣመር የተረጋጋና ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዳይኖር ልትገዳዳር የምትችል ኃይል ናት ይላል።

እናም በባይደን አስተዳደር ውስጥ የሚታመነው ነገር በሚያስፈልግበት ወቅት ቻይናን መጋፈጥ ሲያስፈልግ ደግሞ መተባበር በሚል መርህ ነው።

ቻይናም ቢሆን ተመሳሳይ አቋም ይዛለች። ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንደምትፈልግ ጠቆም አድርጋ የአገሯን ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን ተያይዛዋለች።

በሆንግ ኮንግ ፀረ ዲሞክራሲ አፈናዎች፣ እንዲሁም በብሊንከን የዘር ጭፍጨፋ ነው ተብሎ የተጠራውን የሙስሊም ዜጎቿን አይን ያወጣ ስቃይን በተመለከተ ትችት ለሚሰጥ ሰው ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች።

ቻይና በአሜሪካ ሥርዓት ላይ ያሉ ኢ-ፍትሐዊ ሁኔታዎችን ለማጋለጥ ጊዜዋን ብዙም አታቃጥልም። በዝምታ ነው የምታልፋቸው።

በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወቅት አሜሪካ የኮቪድ-19 ቀውስ ውስጥ መግባቷ እንዲሁም በካፒቶል የተነሳው ነውጥ አሜሪካ በማህበራዊና በምጣኔ ኃብት ዘርፍ አርዓያ ነኝ ብላ የምታስበውን የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው።

እንዲሁ ከላይ ስናየው ሁለቱ አገራት ቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል የሚለው ስያሜ ተገቢ ይመስላል። ነገር ግን ይህንን ማለቱ ጠቃሚ ይሆን?

በዋነኛው ቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት ሶቭየት ሕብረትና አጋሮቿ ከዓለም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የተነጠሉ ነበሩ። እንዲሁም የወጪ ንግዳቸውም ከምዕራባውያኑ በኩል ከፍተኛ ቁጥጥር ነበረበት።

አሁን ቻይና ያላትን አቋም ስናይ በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ አድራጊና ፈጣሪ ናት። የራሷም ምጣኔ ኃብት ከአሜሪካ ጋር በጥብቅ የተጋመደና የተሳሰረ ነው።

የመጀመሪያው የቀዝቃዛ ጦርነት በጦር መሳሪያና በጠፈር ምርምሮች ዙሪያ በቴክኖሎጂ ማን ይበልጣል የሚል እሽቅድምድሞሽና ፉክክሮች ነበሩት። በአሁኑም ወቅት ያለው የአሜሪካ-ቻይና ፉክክር የሰውን ልጅን መፃኢ ዕድል ይወስናሉ የሚባሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስና 5ጂ ጋር ተሳስሯል።

የአሁኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታም የተለየ ነው። በዚያን ቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት ዓለም በሁለት ጎራዎች የተከፈለች ነበረች። ከየትኛውም ጎራ ያልተሰለፉት መሃል ገቦቹ ደግሞ በምዕራባውያኑ ዘንድ ከሶቭየት ሕብረት ወገን ተደርገው ነው የሚታዩት።

በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በብዙ ጎራዎችን ዘንድ ተከፋፍላለች። ሆኖም ራሱን ሊበራል ብሎ የሚጠራው የዓለም ሥርዓትና ተቋማት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አደጋ ላይ ናቸው። ይህም ሁኔታ ቻይና የራሷን የዓለም እይታ እንድትጭን ቦታ ሰጥቷታል።

ሆነም ቀረም ቀዝቃዛ ጦርነት የሚባለው እይታ በመሰረታዊነት ጥልቅ አደጋን ያዘለ ነው።

የሁዋዌ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካና በሶቭየት ሕብረት መካከል የነበረው የፖለቲካ ፍትጊያና፤ በሁለቱም በኩል ከሕጋዊነትንና ተቀባይነት ጋር ተያይዞ የነበረው መካካድ የዜሮ ድምር ነበር።

ሁለቱ አገራት ፊት ለፊት ጦርነት ባይገጥሙም አሜሪካም ሆነ ሶቭየት ሕብረት በተለያዩ አገራት ያደርጓቸው የነበሩ የውክልና ጦርነቶች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

በመጨረሻም የሶቭየት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ጠፋ፤ ተሸናፊም ሆነ። የቻይናና የአሜሪካን ፉክክርና የርዕዮተ ዓለም ብሽሽቅ ያላጤኑት ጉዳይ ውሰጥ ይከታቸዋል የሚሉ አሉ። በተለይም ከመሸነፍ ለመዳን ስትል ቤጂንግ የማትሄድበት መንገድ ሊኖር እንደማይችል ጠቋሚ ነገሮች አሉ።

ነገር ግን ቻይና ሶቭየት ሕብረትን አይደለችም፤ ኃያል አገር ናት። የሶቭየት ሕብረት ያልተጣራ ብሔራዊ ገቢ (ጂዲፒ) ጣሪያ በነካበት ወቅት የአሜሪካን 40 በመቶ ነበር። የቻይና ያልተጣራ ብሔራዊ ገቢ በአስር ዓመት ውስጥ ከአሜሪካ እኩል ይስተካከላል።

ቻይና፣ አሜሪካ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አይታው የማታውቀው ኃያል ተፎካካሪዋ ናት። በሚቀጥሉት አስርት ዓመታትም ግንኙነታቸው ክትትል ያስፈልገዋል።

የዘመናችን ኃያላን ተፎካካሪዎች ናቸው። ታሪካዊ ትንታኔዎችንና ነገሮችን ከአሁን ጋር ለማዛመድ የምንሞክርበትን ሁኔታ ወደ ጎን ብንተወው ይህ ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት አይደለም። አይተነው የማናውቀውና የበለጠ አደገኛም ነው።

በብዙ ዘርፎች ቻይና የአሜሪካ አቻ ተፎካካሪ ናት። ምንም እንኳን ብቸኛ የዓለም ኃያል አገር ባትሆንም ቻይና የደህንነቴ ጉዳይ ይመለከተኛል በምትለው ወታደራዊ ዘርፍም የአሜሪካ ተፎካካሪም ናት።

ለፕሬዚዳንት ባይደን የቻይና ሁኔታ ውስብስብና እንዲህ በቀላል የሚፈታ አይደለም። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም ለቤጂንግ እርስ በርስ የሚጋጩ ሆነው ታይተዋል።

በእስያ-ፓስፊክ ቀጠናዎች ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ አብሮ ለመስራት፣ ፍትሐዊ የሆነ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን እንዴት ቻይና ላይ ጫና ማድረግ ይቻላል? ዲሞክራሲ ላይ ሰብዓዊ መብት ጉዳዮችስ?

ሆኖም እነዚህ ፉክክሮች ስትራቴጂና ጥንቃቄ ያሻቸዋል። ፉክክሮቹ ተጋነው መወራትም ሆነ እንደዚሁ በቀላሉ መታለፍ የለባቸውም። ቻይና እያንሰራራች አሜሪካ እየወደቀች ነው የሚለው የተለመደ አባባል እውነታ ቢኖረውም ሙሉ ገፅታውን አያሳይም።

አሜሪካ ከትራምፕ ቀውስ ወጥታ ማገገምና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደሯ እንዲያንሰራራ ማድረግ ትችላለች? የቀድሞ አጋሮቿንስ በዓለም መድረክ ላይ እምነት የሚጣልባትና ቋሚ ኃይል መሆኗን ማሳመን ትችላለች? አሜሪካ የትምህርትና የቴክኖሎጂ መሰረቷን ማስፋትስ ትችላለች።

ቤጂንግ በብዙ መንገድ የዋሽንግተንን ደወል ነጥቃለች። ነገር ግን ፈላጭ ቆራጭ አካሄዷ ምጣኔ ኃብቷ ላይ እክል ይፈጥር ይሆን? የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲስ ለዘለቄታው የሕዝቡን ድጋፍና ታማኝነት ይዞ ይዘልቅ ይሆን?

ቻይና በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖራትም ደካማም በዚያው ልክ አላት። አሜሪካም ትልቅ የሚባል ደካማ ጎኖች ቢኖራትም ራሷን እንደገና ታላቅ ለማድረግ ቦታው አላት።

ልክ የኮቪድ-19 በአንድ አገር ተወስኖ እንዳልቀረ እነዚህ ቁልፍ የዓለማችን አገራት የሚያከናውኗቸው ነገሮችም ሆነ ውሳኔዎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥን ያመጣሉ።

ረዥም ጎዳና ይመስላል፤ አሁን ጅማሮ ላይ ነው።