በባንግላዴሽ 70 ነብሮችን 'የገደለው' አዳኝ ከ20 ዓመት ፍለጋ በኋላ ተያዘ

በኔፓል የሚገኝ ነብር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሀቢብ ታሉክዳር ይባላል። ሀቢብ ነብር ተብሎም ይጠራል።

ይህንን ስያሜ ያሰጠው ነብር በማደን መታወቁ ነው።

70 ነብሮችን የገደለው አዳኙን ሀቢብን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሶስት የእስር ማዘዣ ወጥቶበት ከ20 ዓመታት አሰሳ በኋላ በፖሊስ እጅ ገብቷል።

ሀቢብ በህንድና በባንግላዴሽ ድንበር መካከል በሚገኝ በሰንዳርባንስ ማንግሮቭ ደን ውስጥ ነበር አደኑን ሲያከናውን የነበረው።

የደን ስፍራው ቤንጋል የተሰኘውን የነብር ዝርያ ከየትኛውም የዓለም ክፍል በላቀ የሚገኝበት ሲሆን ቁጥራቸው እየተመናመነ መጥቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ነብሮች ቀርተውበታል።

በዓለም ዙሪያ ህገ ወጥ በሆነ መልኩ የቤንጋል ነብሮች ስጋና አጥንት ሳይቀር ንግድ መጧጧፍ ለቁጥራቸው መመናመን ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።

ታዲያ ነብር አዳኙ ሀቢብ "ለረጅም ጊዜ ሲሸሽ ነበር" ሲሉ የፖሊስ አዛዡ ሳይደር ራህማን ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የ50 ዓመቱ ሀቢብ ነብር ገዳይ ከመሆኑ በፊት ማር በማምረት ነበር ስራውን በደን ውስጥ የጀመረው። አብዱስ ሰላም የተባለ ማር ቆራጭ ነብር አዳኙ ሀቢብ "በአከባቢው ሰው በእኩል የሚከበርና የሚፈራ ነበር" ሲል አስተያየቱን ለኤ ኤፍ ፒ ሰጥቷል።

" ደን ውስጥ ብቻውን ከነብር ጋር የሚጋፈጥ አደጋኛ ሰው ነው" ሲልም አክሏል።

የፖሊስ መኮነኑ አብድልመናን ለመገኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት ፖሊስና የደኑ አስተዳደር ሀቢብን ለዓመታት ሲያድኑት መቆየታቸውን ገልጸዋል።

"ከአመታት በፊት የተቀመጠውን ወደ ደኑ የመግባት ክልከላ እየተላለፍ የዱር እንስሳትን ሲገል ነበር። ክስ እያለበት እንኳን ድርጊቱን አላቆመም ነበር። ይህንን ወንጀል የሚፈጽመው ከወሮ በላ ቡድን አባላት ጋር በመሆን ነው" ሲል አስረድቷል።

ከሀያ ዓመታት አሰሳ በኃላ የተያዘው ነብር አዳኙ ሀቢብ ባለፈው ቅዳሜ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።