ናኦሚ ኦሳካ ከፈረንሳይ ውድድር ራሷን አገለለች

ናኦሚ ኦሳካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአለም ቁጥር ሁለት የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ናኦሚ ኦሳካ ከፈረንሳይ ውድድር ራሷን እንዳገለለች አስታወቀች።

ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለመናገር ፈቃደኛ ካልሆነች ትታገዳለች የሚል ውዝግብን ተከትሎ ነው በፈረንሳይ ኦፕን እንደማትወዳደር ያሳወቀችው።

ይህንን ባሳወቀችበት የትዊተር መልዕክትም ናኦሚ በጭንቀት (ዲፕረሽን) ህመም እየተሰቃየች እንደሆነ አስፍራለች።

ህመሟም የጀመረው ከሶስት አመት በፊት በሜዳ ቴኒስ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን የመጀመሪያዋን ግራንድ ስላም ካሸነፈች ጀምሮ ነው።

የ23 አመቷ አትሌት የአዕምሮ ጤንነቷን ለመጠበቅ በሮላንድ ጋሮስ ጋዜጣዊ መግለጫ አልሳተፍም ያለችው ባለፈው ሳምንት ነበር።

ባለፈው ሳምንት እሁድ ከሮማኒያዊቷ ፖትሪሺያ ማሪያ ቲግ ጋር በነበረው ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀችበት ጨዋታ ተከትሎ ከሚዲያዎች ጋር ቆይታ አላደርግም በማለቷ 15 ሺህ ዶላር ተቀጥታለች።

በዚያኑ ቀን የግራንድ ስላም ውድድር አዘጋጆች ባወጡት የጋራ መግለጫ አትሌቷ ሚዲያ አላናግርም በሚል ባህርይዋ ከቀጠለች ከጨዋታዎች እንደምትታገድ አስጠንቅቀው ነበር።

አትሌቷም በትናንትናው ዕለት ከፈረንሳይ ኦፕን ራሷን እንዳገለለች ገልፃ "ለተወሰነ ጊዜም ከሜዳ ራሴን አርቄያለሁ " ብላለች።

"ትክክለኛው ወቅት ሲመጣ ከውድድር አዘጋጆች ጋር ለአትሌቶች፣ ለሚዲያዎችና ለተመልካቾች በምን መንገድ ውድድሮችን ማሻሻል እንችላለን የሚለው ላይ መወያየት እፈልጋለሁ' ብላለች።

የፈረንሳይ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጊለስ ሞሬቴን የናኦሚን ራሷን ከውድድር ማግለል አስመልክቶ "አሳዛኝ" ብለውታል።

"ናኦሚ በገጠማት ሁኔታ ሃዘን ተሰምቶናል። በፍጥነትም እንድታገግም ምኞታችንን እየገለፅን በሚቀጥለው አመት ውድድራችን እናያታለን ብለን እንጠብቃለን" ብለዋል ።

"ሁሉም የግራንድ ስላምስ ውድድሮች ማለት ደብልዩ ቲ ኤ፣ ኤቲፒና አይቲኤ ለአትሌቶች ጤና ቅድሚያ በመስጠት በሌሎችም ዘርፎች አትሌቶች የሚሻሻሉበትን መንገድ እንቀይሳለን። ከዚህም ጋር ተያይዞ አትሌቶች ከሚዲያዎች ጋር ያላቸው ግንኙነቶች እንዲሻሻሉ ስንሰራ ነበር። አሁንም እንሰራለን" በማለት አስረድተዋል።