ጀርመን ናሚቢያን ቅኝ በገዛችበት ወቅት የዘር ጭፍጨፋ ማካሄዷን አመነች

በስምምነቱ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ጀርመን ናሚቢያን ቅኝ በገዛችበት ወቅት የዘር ጭፍጨፋ ማካሄዷን አምናለች።

ካሳ በሚመስል ሁኔታም የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ከሰሞኑ አስታውቃለች።

ጀርመን ናሚቢያን በቅኝ ግዛት የያዘችው በአውሮፓውያኑ ከ1884-1915 ወቅት ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ናሚቢያውያንን ጨፍጭፋለች።

የዘር ጭፍጨፋ የተካሄደባቸው የሄረሮና የናማ ህዝቦች ናቸው። በዚህ ጭፍጨፋም 80 በመቶ የሚሆኑት የነዚህ ማህበረሰብ አባላት ተጨፍጭፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሄይኮ ማስ በዛሬው ዕለት እንዳመኑት የጅምላ ግድያውንም ሆነ የዘር ጭፍጨፋ መፈፀሙን አምነዋል።

"የጀርመንን ታሪክን ፈትሸን በአሁኑ ወቅት የሞራል ኃላፊነት እንዳለብን እንረዳለን። ናሚቢያውያንም እንዲሁ በቀጥታ የዘር ጭፍጨፋው ተጠቂ የሆኑ የልጅ ልጆችን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ጀርመን "የዘር ጭፍጨፋው ጥቃት ሰለባዎች ምን ያህል ለማይሽር ቁስልና ህመም እንዳደረገቻቸውም እንረዳለን።"

በማለትም ከዚህም ጋር በተያያዘ ለአገሪቱ የልማት ፕሮግራም የሚውል 1.34 ቢሊዮን ዶላር አገራቸው መለገስ እንደምትፈልግ ገልፀዋል።

ገንዘቡም በጭፍጨፋው ተጠቂ ለሆኑት ማህበረሰቦች ለልማት፣ የጤና ተቋማትን ግንባታና ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚውል ሲሆን በ30 አመታትም ውስጥ የሚለገስ ነው ተብሏል።

"አሁን ላይ ቆመን ታሪክን ወደ ኋሊት ስንመለከት በናሚቢያ ላይ የተፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ ነበር። በቅጭ ግዛት የተፈፀሙ ድርጊቶችን ልንሸፋፍናቸው አይገባም። ልንወያይባወቸው" ይገባል በማለትም በዛሬው መግለጫቸው ዳስሰዋል።

የናሚቢያ መንግሥት ቃለ አቀባይ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ጀርመን የዘር ጭፍጨፋ ተካሂዷል ብላ እውቅና መስጠቷ "በትክለኛው መንገድ የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው" ብለውታል።

ነገር ግን አንዳንድ የአገሪቱ ባህላዊ መሪዎች መንግሥትን በገንዘብ ራሱን የሸጠ ብለው ከመወንጀል በተጨማሪ የጀርመን መንግሥትን የእርዳታ ገንዘብ መቀበል የለብንም በማለት በፅኑ አውግዘውታል።