ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ኢሲያዊያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት ለምን ጨመረ?
ኢሲያዊያን ዝርያ ያላቸው ሰዎች በአሜሪካ ጥቃት በርክቶባቸዋል፡፡ ይህም የሆነው ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ነው፡፡
ዛሬም ድረስ ነገሩ እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ አልመጣም፡፡
በዚህም የተነሳ ጆ ባይደን አዲስ ረቂቅ ሕግ እንዲወጣ አድርገዋል፤ ፊርማቸውንም አኑረውበታል።
የፈረሙበት ረቂቅ ሕግ ኢሲያዊያን ጥቃት እየጨመረ በመምጣቱ ይህንኑ ለመግታት ካስቻለ በሚል ነው፡፡
መቼ ለታ አንድ የታይላንድ ጎልማሳ መሬት ላይ ተገፍትረው ተጥለው ሞተዋል፡፡
በቀደም አንድ የፊሊፒንስ ዝርያ ያለው አሜሪካዊ በሴንጢ ፊቱ ተቆራርጧል፡፡
ባለፈው አንዲት ቻይናዊት ሴት በጥፊ ተመትታ እሳት ተለኩሶበታል፡፡
የዛሬ ዓመት ገደማ በአንድ ምሽት በኢሲያዊያን የውበት ሳሎን ውስጥ ስምንት የኢሲያ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ተገድለዋል፡፡
እነዚህ በሙሉ በቅርብ ጊዜ በተለይም የኮቪድን ወረርሽኝ ተከትሎ በአሜሪካ ምድር የደረሱ ጥቃቶች ናቸው፡፡
በቅርብ ወራት ደግሞ ፖሊስ በርካታ ክሶች ደርሰውታል፡፡
በተለይም በቃላት ዝርጠጣና ማንጓጠጥ፣ በድብደባ፣ እንዲሁም መንገድ ላይ በአደባባይ ጭምር የተተፋባቸው ኢሲያዊ መልክ ያላቸው አሜሪካዊያን ለፖሊስ አቤት ብለዋል፡፡
የመብት ተቆርቋሪዎች ይህ የጥላቻ ወንጀል ነው ይላሉ፡፡ በኢሲያዊያን ላይ ጥላቻው የበረታው ደግሞ ኮቪድ ወረርሽኝን ያመጣችሁብን እናንተ ናችሁ ከሚል እሳቤ ስለሚመነጭ ነው፡፡
የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ወረርሽኙ የመጣ ሰሞን በኢሲያዊ መልክ ባላቸው ዜጎች ላይ ጥቃት ሊበረታ እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር፡፡
የ2020 የጥላቻ ጥቃቶች ሪፖርት ለጊዜው ይፋ ባይሆንም በ2019 የጥላቻ ጥቃት አሐዝ ባለፉት 10 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
ስቶፕ አፒሄት የተባለ አንድ በመብት ላይ የሚሠራ ቡድን ባለፈው ዓመት ብቻ 3ሺ የሚጠጉ ሪፖርቶች እንደደረሱት ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህ ሁሉ አቤቱታዎች የደረሱት ከኢሲያዊያን ሲሆን መልከ ብዙ ጥቃቶች ከተሰነዘረባቸው በኋላ ለተቋሙ አቤት ያሉ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በኢሲያዊያን ላይ የጥላቻ ጥቃቶች አሳሳቢ በሚባል ደረጃ እየጨመሩ ነው ሲል ዘገባ አውጥቷል፡፡
አንዳንድ ግዛቶች ችግሩን ለመቅረፍ የተናጥል እርምጃ ጀምረዋል፡፡
ኒውዮርክ ከተማ ይህን የሚከታተል ልዩ ኃይል ያቋቋመች ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ 27 ከፍተኛ ጥቃቶች መድረሳቸውን ሰንዳለች፡፡
በኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ ፖሊስ ‹ቻይናታውን› በሚባለው ሰፈር ልዩ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) እስከማቋቋም ደርሷል፡፡
ነገሩ እየተስፋፋ በመሄዱ ዕውቅ አሜሪካዊያን ይህ ዘረኝነት ጥቃት እንዲቆም ጥሪ ማቅረብም ጀምረዋል፡፡
እንዴት በአንድ ጊዜ በኢሲያዊያን ላይ ይህ ሁሉ የጥላቻ ጥቃት ሊደርስ ቻለ? ነገሩስ ለምን እያደገ መጣ ለሚለው ብዙ መላምቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡
አሜሪካዊያን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ሕይወታቸው ስለተመሰቃቀለ ይህን ወረርሽኝ ያመጡት ደግሞ የኢሲያ ሰዎች ናቸው ብለው በተሳሳተ መልኩ መረዳታቸው አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይገመታል፡፡
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ ነገሩን ያባባሱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው ይላሉ፡፡
ትራምፕ በንግግራቸው ጸረ ቻይና አመለካከቶችና ዘረኝነቶች ይንጸባረቁ ስለነበር፣ በተለይም ወረርሽኙን ‹የቻይና ተህዋሲ› እያሉ ይጠሩት ስለነበር ደጋፊዎቻቸው ኢሲያዊያንን ሲያዩ ደማቸው መፍላት እንደጀመረ ይናገራሉ፡፡
ባይደን በበኩላቸው እንዲህ ያሉ ቃላት ጥላቻን ስለሚያነግሱ ማንም ሰው ኮቪድን ‹የቻይና ተህዋሲ› ወይም ‹ኩንግ ፍሉ› በሚል ቃል እንዳይጠቀም የሚከለክል ሕግ ላይ ፈርመዋል፡፡
ይህን ያደረጉትም ነጩ ቤተ መንግሥት በገቡ በመጀመርያው ሳምንት መሆኑ ለነገሩ የሰጡት ቦታ የሚያሳይ ነበር፡፡
በግንቦት 20 ደግሞ ኮቪድ19 ክራይም አክት የተሰኘ ረቂቅ ላይ ፈርመዋል፡፡
ይህ ረቂቅ ለፌዴራል አቃቢ ሕግ በዚህ የኢሲያዊያን ጥላቻ ዙርያ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ በጀት የሚፈቅድ ሲሆን ግዛቶችም የጥላቻ ጥቃቶችን እንዲከላከሉና ሰፊ ሥራ እንዲሠሩ የሚያግዝ ድጎማን ይሰጣል፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላም ግን ነገሩ መሻሻል አልታየበትም፡፡ በአሜሪካ ኢሲያዊያን አሁንም ይንጓጠጣሉ፤ ይደበደባሉ፣ ተገድለው ይጣላሉ፡፡ ምናልባት ትልቁ ሥራ መሠራት ያለበት አስተሳሰብ ላይ ሳይሆን አልቀረም፡፡