ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ በበሽታ የሚሞቱ ሰዎችን መጠን ለማወቅ መመሪያ አዘጋጀች
ኢትዮጵያ በአገር አፍ ደረጃ በበሽታ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን መጠን ለማወቅ የሚያስችል የቅኝት መመሪያ ማዘጋጀቷን ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ካገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።
በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሞት መጠን ለማወቅ የሚያስችል የቅኝት መመሪያ ለማዘጋጅት መነሻ የሆነው የኮሮኖቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑም ተገልጿል።
መመሪያወው በማህበረሰቡ ውስጥ በበሽታ የሚሞቱ ሰዎችን ጭምር ማካተት እንደሚኖርበት ታምኖ የአገሪቱን የሞት መጠን የሚያሳውቅ መመሪያ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
በተለይም እንዲህ አይነት ወረርሽኞች ሲከሰቱ የሞቱን መጠን በትክክል ለማወቅ፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የሞት መጠን ለመገምገም፣ በሽታው የትኛውን የማህበረሰብ ክፍል በፆታ፣ በእድሜና ሌሎች መስፈርቶች አስመልክቶ የትኛውን አካል ነው እያጠቃ ነው የሚለውን በተመለከተ መመሪያው ምላሽ ይሰጣል ተብሏል።
መመሪያው ይፋ የተደረገው ግንቦት 11፣ 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ነው።
መመሪያው ይፋ መሆኑን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ መስጠት ዳይሬክቶሬት የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ዳሰሳ እና ምላሽ መስጠት ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ሮዚና ታሪኩ ከመረጃዎች አሰባሰብና መለኪያ ጋርም ተያይዞ ወሳኝ የሚባሉ ጉዳዮች በመመሪያው መካተታቸውን አስታውቀዋል።
መመሪያው መጠናቀቁን አስመልክቶ አዳማ በነበረው ዝግጅት ላይ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንደተናገሩት መመሪያው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጉዳት ሳያደርሱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
መመሪያውን በማዘጋጀቱ በኩል የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ የክልሎች የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር እና የአጋር ድርጅት ተወካይ ባለሙያዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውም ከመረጃው መረዳት ተችሏል።