ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ የብዝሓ ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ አስመረቀች
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ያስገነባውን 7.3 ሜትር የብዝሓ ሳተላይት መረጃ መቀቢያ ጣቢያ በዛሬው ዕለት ግንቦት ግንቦት 7፣ 2013 ዓ.ም አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በምርቃቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ካሏት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ውጭ በሌሎች አገሮች ካሉ አምስት ሳተላይቶች መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችል ጣቢያ ነው ብለዋል።
በቻይና፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ እና በአውሮፓ ህብረት ከሚተዳደሩ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መረጃ ለመቀበል የሚያስችል የመረጃ ልውውጥ ስምምነትም ተደርሷል።
የዚህ ፕሮጀክት መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምልከታ ሳተላይት ከመምጠቋ በፊት የሚገኘው የሳተላይት መረጃ ብቻውን ኢትዮጵያን ለሚያክል ትልቅ አገር በቂ እንዳልሆነ እሳቤ ውስጥ በማስገባት ይህ ፕሮጀክት እንደተጠነሰሰ ተገልጿል።
ሌሎች አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ ያንን አቅም እስክትገነባ ድረስ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ጣቢያው ተገንብቷል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ሶስት አመት እንዲሁም 3ሚሊዮን ዩሮ ገደማ መፍጀቱንም በምርቃቱ እለት ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከአርባ የማያንሱ የተቋሙ ሳይንቲስቶችና መሃንዲሶች ተሳትፈውበታል።
የጣቢያውን ፋይዳ አስመልክቶ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያንና የጎረቤት ሀገራት የመረጃ ፍላጎትን ለማሟላት፣ የስራ እድል መፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ጣቢያው በአሁኑ ወቅት አምስት የመሬት ምልከታ ሳተላይት መረጃዎችን የሚቀበል ቢሆንም በቀጣይነት ግን ከሜትሮሎጂ ሳተላይቶች መረጃ መቀበል እንዲችል የማስፋፊያ ስራ እንደሚሰራም ተጠቁሟል። የሳተላይቶቹን ቁጥር አሁን ካለበት አምስት የመጨመር እቅድም እንዳለ ተገልጿል።
ከሳተላይት የሚወሰዱ መረጃዎች ለግብርና ስራዎች፣ ለተፈጥሮ አደጋዎች ትንበያና ቅድመ ጥንቃቄ፣ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና ለማዕድን አሰሳ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከግብርና ሚኒስቴርም ጋር ሰፊ ስራ እንደተሰራና ለአስር አመት የሚሆን ፕሮግራም እንደተነደፈም በምርቃቱ ወቅት ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው ጣቢያውን በመረቁበት እለት "የዚህ ጣቢያ መገንባት የመረጃ አይነትና ብዛትን በማሟላት ኢትዮጵያ በህዋ ዘርፍ ያላትን ጥንካሬ ከፍ የሚያደርግ እድል እንደሚፈጥር" ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችላትን የዲጂታል ስትራቴጂ ቀርፃ እየሰራች ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ጣቢያው በስትራቴጂው ከተካተቱ ከግብርና እሴት ማመንጨት እና ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ መደግፍ የሚሉትን ለማስፈፀም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ተቋሙ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ያመጠቀ ሲሆን ከመጠቀችበት ዕለት አንስቶ የቁጥጥርና መረጃ የመቀበል ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ሳተላይቷ ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረገ የትብብር ስምምነት አማካኝነት የበለፀገችና የመጠቀች ሲሆን ከሳተላይቷ የሚገኝ መረጃም ለልዩ ልዩ ሃገራዊ የልማት አገልግሎት ስራዎች እየዋለ እንደሚገኝም ተገልጿል።