በሞዛምቢክ ጥቃት ነፍስ አድን ሰራተኞች ለነጮችና ለውሾች ቅድሚያ ሰጥተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
መጋቢት ወር ላይ ጂሃዲስቶች አደረሱት በተባለ ጥቃት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ለነጮች ቅድሚያ መስጠታቸውን አለም አቀፉ የመብት ተሟጋቾች ድርጅት አምነስቲ አስታውቋል።
አምነስቲ የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ሪፖርት ከነጮች በተጨማሪ ሁለት ውሾችንም ከጥቃቱ ለማዳን በሄሊኮፕተር እንደተወሰዱ ነው።
ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ከጥቃቱ ለመዳን በሆቴል ጀርባ እንደተሸሸጉም ተናግረዋል።
"የነፍስ አድን ሂደቱ በዚህ መንገድ ዘርን መድልዎ አድርጎ መታቀዱ ከፍተኛ ስጋትን አጭሮብናል። በዚህም ሂደት ለነጭ ሰራተኞች ቀድሚያ መሰጠቱንም መረጃዎች ደርሰውናል" በማለት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀጠናው ዳይሬክተር ዴፕሮስ ሙቼና ተናግረዋል።
አምነስቲ ጥቃቱን ለማምለጥ በሆቴሉ ውስጥ ተደብቀው ከነበሩ 220 ሞዛምቢካውያን መካከል 11ዱን ያናገረ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አምስቱ ጥቃት ደርሶባቸው የተረፉ ናቸው ብሏል።
"ከጥቃቱ ለማምለጥ በሚል በሆቴሉ ተደብቀን የነበርነው 220 ሰዎች ነበርን። ነጮቹ 20 ብቻ ነበሩ። በአብዛኛው ጥቁርና የአካባቢው ሰዎች ነበርን። ነጮቹን በሄሊኮፕተር መጥተው የወሰዷቸው ሲሆን እኛን ግን እዛው ትተውን ሄዱ" በማለት ከጥቃቱ የተረፈ ግለሰብ ለአምነስቲ ተናግሯል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የተዋቸው ግለሰቦችም በእግራቸው ከሆቴሉ በእግራቸው ለማምለጥ ሲሞክሩ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
ይሄም ሁኔታ ምርመራ እንዲደረግበት ድርጅቱ አሳስቧል።
"በእንዲህ አይነት ጥቃት ላይ ግለሰቦችን በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ትቶ መሄድ ዘረኝነት ነው። የሰላማዊ ሰዎችን ጥበቃ ጋር የሚጣረስም ነው። ይሄ ሁኔታ ሳይመለስ መቅረት የለበትም" በማለት ዴፕሮስ ሙቼና ገልፀዋል።
የነፍስ አድን ስራውን እያከናወነ ነበር የተባለው የግል ኩባንያው ድያክ አድቫይዘሪ ግሩፕ በበኩሉ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገረው የተባለው ነገር "ሁሉም ትክክለኛ እንዳልሆነና" በቅርቡም መግለጫ እንደሚያወጣ አስታውቋል።












