ሕዋ ሳይንስ: ብዙ የተባለለት የቻይና ሮኬት ስብርባሪ ጉዳት ሳያደርስ ውሃ ላይ ወደቀ

ቻይና ወደ ሕዋ ያስወነጨፈችው ሮኬት ስብርባሪዎች በተዘጋጀላቸው ቦታ ሕንድ ውቂያኖስ ላይ ማረፋቸውን አስታውቃለች።

የሮኬቱ አብዛኛዎቹ ክፍሎች ወደ ምድር በሚምዘገዘጉበት ወቅት ተቃጥለው አየር ላይ የቀሩ ሲሆን አንዳንድ ስብርባሪዎች ግን በታሰበው ቦታ ላይ ማረፋቸውን የቻይና ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

የአሜሪካ እና አንዳንድ የአውሮፓ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ያልነበረውን ሮኬት ሂደት ሲከታተሉት ነበር።

'ማርች 5ቢ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ሮኬት ባሳለፍነው ወር መገባደጃ ላይ ነበር ቻይና በሕዋ ላይ ለመስራት ላሰበችው ማዕከል የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ይዞ ነው ወደ ህዋ የተወነጨፈው።

18ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሮኬት በአስርት ዓመታት ውስጥ ቁጥጥር ሳይደረግበት ወደ ምድር የሚወድቅ ግዙፍ ቁስ ነው ተብሎ ነበር።

የዚህ ሮኬት ስብርባሪ አካላት ደግሞ በትክክል መቼ እና የት እንደሚወድቁ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም መባሉ ስጋትን ፈጥሮም ነበር።

የአሜሪካ የሕዋ ማዘዢያ ጣቢያ ባወጣው መግለጫ ማርች 5ቢ በአረቢያን ባህረሰላጤ በኩል ወደ ምድር መግባቱን አረጋግጧል። አክሎም ‘’የሮኬቱ ስብርባሪ ግን የውሃ አካል ላይ ጉዳት ማድረስ አለማድረሱ አልታወቀም’’ ብሏል።

አሜሪካ ቀደም ብላ ባወጣችው መግለጫ የሮኬቱን አቅጣጫ እና አካሄድ በቅርበት እየተከታተለች እንደሆነ በመግለጽ ተኩሳ የመጣል እቅድ ግን እንደሌላት አስታውቃ ነበር።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስቲን "ሮኬቱ ጉዳት ሳያስከትል እንደሚወድቅ ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

ነገር ግን የሕዋ ሳይንስ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሮኬቱ ስብርባሪዎች ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ የመውደቃቸው ዕድል በጣም ዝቅተኛ ነው።

የመሬት አካል አብዛኛው ክፍል በውሃ የተሸፈነ እና አብዛኛው የምድራችን ክፍል ሰዎች የማይኖርቡት መሆኑ ለዚህ መቂ ምክንያት ነው ይላሉ።

ከዚህ በፊት በተመሳሳይ አንድ የቻይና መንኩራኩር ስብርባሪ ከታሰበለት ጊዜና ቦታ ውጪ ወደ ምድር ከባቢ አየር በመግባት በአንዲት የአይቮሪ ኮስት የገጠር መንደር ውስጥ ወድቆ ነበር።

ቻይና የሮኬቱን ስብርባሪዎች መውደቂያ ቦታ እና ትክክለኛ ሰአት መቆጣጠር አለመቻሏ ግድየለሽነቷን የሚያሳይ ነው የሚሉ ወቀሳዎችን ያስከተለባት ሲሆን አገሪቱ ግን ስብርባሪዎቹ ዓለማቀፍ የውሃ ክልል ውስጥ እንደሚወድቅ አውቅ ነበር ብላለች።

በአሁኑ ጊዜ በህዋ ምህዋር ላይ የሚገኘው ብቸኛው ዓለም አቀፍ የህዋ ምርምር ጣቢያ፣ በእንግዝኛ ምሕጻሩ አይኤስኤስ (ISS) ነው። ይሁንና ቻይና በዚህ ጣቢያ ውስጥ አልታቀፈችም።

ለዚህም ነው ቻይና በአውሮፓውያኑ 2022 የራሷ የህዋ ጣቢያ ግንባታን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና የምትለው።