ሲኖፋርም፡ የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ

የሚከተብ ሰው

የፎቶው ባለመብት, EPA

በቻይና መንግሥት በሚተዳደረው ሲኖፋርም ኩባንያ የተመረተው የኮቪድ ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል የዓለም ጤና ድርጅት ይሁንታውን ሰጠ።

በድርጅት ይሁንታ ያገኘ ከምዕራባውያን ውጭ የተሠራ የመጀመሪያ ክትባት ሆኗል፡፡

ፈቃድ ከማግኘቱም በፊት ክትባቱ በቻይና እና በሌሎች አካባቢዎች ለሚሊዮን ሰዎች ተሰጥቷል፡፡

የፋይዘር፣ የአስትራዜኔካ፣ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና ሞደርና ክትባቶች ቀደም ብለው ከዓለም የጤና ድርጅት ዕውቅና አግኝተዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት ግን ቀደም ሲል በተናጠል ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውሉ የቻይናውያን ክትባቶችን ፈቅደዋል፡፡

ቀደም ሲል አነስተኛ መረጃ የተለያዩ ብቻ መለቀቁን ተከትሎ የቻይና ክትባቶች ውጤታማነት አልታወቀም ነበር፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት አርብ ዕለት የሲኖፋርም ክትባትን "ደህንነት፣ ውጤታማነት እና ጥራት" አረጋግጧል ብሏል፡፡

የክትባቱ ፈቃድ ማግኘት "የጤና ሠራተኞችን እና ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ለመከላከል የሚያስፈልገውን የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነት የማፋጠን አቅም አለው" ብሏል ድርጅቱ።

ክትባቱ ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች በሁለት ዙር እንዲሰጥ ይመክራል፡፡

ሌላኛው ቻይና ሠራሽ ክትባት ሲኖቫክ በሚቀጥሉት ቀናት ውሳኔ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የሩሲያ ስፑትኒክም በግምገማ ላይ ይገኛል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ይሁንታ መስጠቱ ምን ይጠቅማል?

ከዓለም ጤና አካል የተሰጠው አረንጓዴ መብራት ክትባት ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ስለመሆኑን ለተቆጣጣሪዎች ማረጋገጫ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ውሳኔው ሃገራት "የራሳቸውን የቁጥጥር ደንብ ለማፋጠን ድፍረት ይሰጣቸዋል" ብለዋል፡፡

ክትባቱ በበለፀጉ እና በድሃ አገራት መካከል ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲኖረው ለማድረግ ባለፈው ዓመት በተቋቋመው ዓለም አቀፉ የኮቫክስ መርሃግብር ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ማለት ነው፡፡

ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለውን የቻይና ክትባት ይሁንታ ማግኘቱ የአቅርቦት ችግሮች ላጋጠመው መርሃግብር ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዕውቅና ከመስጠቱ በፊትም ቢሆን የሲኖፋርም ክትባት በግምት 65 ሚሊዮን ዶዝ መሰጠቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከቻይና በተጨማሪ ክትባቱን ኤምሬትስ፣ ፓኪስታን እና ሃንጋሪ እየተጠቀሙበት ነው።

ለአስቸኳይ ጥቅም ክትባቱን የጸደቀው የአለም ጤና ድርጅት የቴክኒክ አማካሪ ቡድን የቅርብ ጊዜ ክሊኒካዊ መረጃዎችን እና የምርት ሂደቶችን ከገመገመ በኋላ ነው።

ክትባቱ ምልክት ላሳዩ እና ታምመው ሆስፒታል ለገቡት ውጤታማነቱ 79 በመቶ እንደሆነ ተገምቷል፡፡

በክሊኒካዊ ሙከራዎች ወቅት ከ 60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው ለዚህ የዕድሜ ቡድን ያለው ውጤታማነትን ማወቅ አልተቻለም ብሏል ድርጅቱ። ሆኖም ክትባቱ ዕድሜያቸው ከፍ ባሉ ሰዎች ላይ በተለየ መንገድ ይሠራል ብሎ ለማሰብ ምንም ምክንያት እንደሌለ ተናግሯል፡፡

በሌላኛው የቻይናው ሲኖቫክ ክትባት ላይ ውሳኔ ላይ ገና አልተደረሰም፡፡ የድርጅቱ ባለሙያዎች አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ተጨማሪ መረጃዎችን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ከቻይናው ክትባቶች ዋና ዋና ጠቀሜታዎች መካከል እንደ አስትራዜኔካ ክትባት ሁሉ በመደበኛ ማቀዝቀዣ ውስጥ ሊቀመጡ መቻላቸው ነው፡፡