የ25 ዓመቷ ማሊያዊት በአንዴ የዘጠኝ ልጆች እናት ሆነች

የፎቶው ባለመብት, MALI'S HEALTH MINISTRY
የ25 ዓመቷ ወጣት ማሊያዊት የዘጠኝ መንቶች እናት መሆኗ ተሰማ።
ወጣቷ የእርግዝና ክትተል በምታደርግበት ወቅት ከሁለት በላይ ልጆች በማሕፀኗ መሸከሟ ቢታወቅም ዘጠኝ መሆናቸውን ግን የለየ አልነበረም።
ሐሊማ ሲሴ ዘጠኙን ልጆቿን የተገላገለችው በሞሮኮ ነው።
የማላዊ መንግሥት ወደ ሞሮኮ ሄዳ የተሻለ ሕክምና እና ክብካቤ እንድታገኝ ረድቷታል።
አምስት ሴቶች እና አራት ወንዶች ልጆችን በቀላል ቀዶጥገና የወለደችው ሐሊማ በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የማላዊ ጤና ሚኒስትር ተናግረዋል።
ዘጠኝ መንቶችን መውለድ የተለመደ አይደለም፤ እንዲሁም በእርግዝና ወይንም ከወሊድ በኋላ በሚኖር የጤና ችግር ምክንያት የተወሰኑት ልጆች ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።
የሞሮኮ ጤና ሚኒስትር ቃል አቀባይ ራቺድ ኮድሃሪ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ በአንድ ጊዜ ዘጠኝ ልጆች የተወለዱበትን አጋጣሚ እንደማያስታውሱ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የማሊ ጤና ሚስትር ፋንታ ሲቢ፣ በሁለቱም አገራት የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እናቲቱ በሰላም በመገላገሏ የ'እንኳን ደስ አላችሁ' መልዕክት አስተላልፈዋል።
በማሊ የወ/ሮ ሲሲ እርግዝና ለበርካቶች አግራሞትን ጭሯል።
መጀመሪያ ላይ ሰባት ልጆችን ማርገዟ ተገምቶ እንደነበር ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ለእናቲቱ ጤንነት እና ሕጻናቱ በሰላም ወደዚህች ምድር እንዲመጡ ያላቸውን ስጋት ከገለፁ በኋላ የማሊ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል።
እናቲቱ ለሁለት ሳምንታት በማሊ ሆስፒታል ውስጥ ከቆየች በኋላ ወደ ሞሮኮ እንድትሄድ ተወስኗል።
በሞሮኮ ሆስፒታል ውስጥ ለአምስት ሳምንት ከቆየች በኋላ ማክሰኞ ዕለት በሰላም ዘጠኝ ልጆቿን እንደወለደች የጤና ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሲሲ በሞሮኮ ከተወሰነ ሳምንታት ቆይታ በኋላ ወደ ማሊ ትመለሳለች ተብሏል።












