አፕል የተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፌ አልሰጥም ማለቱን ፌስቡክ ተቃወመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አይፎንና አይፓድ አምራቹ ግዙፉ አፕል ኩባንያ ከሰሞኑ ያመጣው አንድ ቴክኖሎጂ ፌስቡክን አስቀይሟል።
አዲሱ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች መተግበሪያዎችን [አፕሊኬሽን] ስልካቸው ላይ ሲጭኑ መረጃቸው እንዳይሰበሰብ የሚያስችል ነው።
ለምሳሌ የአይፎን 12 [ከተመኙ አይቀር] ባለቤት ኖት እንበል። ከዚያ ፌስቡክ ስልክዎ ላይ መጫን ፈለጉ። ፌስቡክን ካለበት አፈላልገው ወደ ስልክዎ ሲያወርዱ አንድ መልዕክት ይደርስዎታል።
መልዕክቱ እንዲህ ይነበባል፡ 'ይህ መተግበሪያ ስለ እርስዎ መረጃ እንዲሰበስብ ይሻሉ? ካልሆነ ይህን ይጫኑ።'
ይህ ጉዳይ ነው ፌስቡክን ያስቆጣው። ምክንያቱም የፌስቡክ ዋነኛ ገቢ ማስታወቂያ ነው። ማስታወቂያ ለተጠቃሚዎች የሚለቀው ደግሞ በድብቅ በሚሰበስበው መረጃ ነው።
ምንም እንኳ ትርፋማው ድርጅት ፌስቡክ ይሁን እንጂ ሌሎችም ኩባንያዎች በአፕል ድርጊት ደስተኛ አይመስሉም።
ያው ደስተኛው የአይፎንና አይፓድ ባለቤትና ተጠቃሚው ብቻ ነው።
ፌስቡክ ስልክዎ አሊያም ኮምፒውተርዎ ላይ ካለ በይነ መረብ ላይ ምን እያደረጉ እንዳሉ ሊያውቅ ይችላል።
ለምሳሌ አንድ በልክዎ የተሠራ ጫማ አይተው ወደዱት እንበል። ወደ በይነ መረብ ዓለም ገብተው ይህን ጫማ ጎልጉለው ቤቴ ድረስ ይምጣልኝ ብለው አዘዙ።
በበነጋው ወደ ፌስቡክ መንደር ሲገቡ የሚያዩትና የሚሰሙት ሁሉ ጫማ ጫማ [አዲስ ጫማ] ቢልዎ አይግረምዎ።
ይህ የሚሆነው ፌስቡክ ወደ ሄዱበት ከኋላ ኋላ እየተከተለ በቴክኖሎጂ አማካይነት ስለሚሰልል ነው።
ታድያ አይኦኤስ 14.5 [የአይፎንና አይፓድ መንቀሳቀሻ ሶፍትዌር] ይህን ለመመከት ቆርጦ ተነስቷል።
በፊት በፊት አንድ መተግበሪያ ስልክዎት ላይ ሲጭኑ መረጃዎን እንሰብስብ ወይ የሚል ምርጫ አይመጣልዎትም ነበር።
አዲሱ አይኦኤስ 14.5 በግላጭ ይህን ይጠይቃል። መቼም 'አዎ መረጃዬ ይበርበር' እንደማይሉ ይታወቃል።
አንድ ፌስቡክ የተስማማበት ጥናት ተሰርቶ 80 በመቶ ተጠቃሚዎች "ኧረ በፍፁም" እንደሚሉ አሳይቷል።
የመረጃ ጥበቃን ለኔ ተዉት እያለ ሁሌም የሚፎክረው አፕል ትርፍ የሚያገኘው ቁሳቁስ በመሸጥ እንጂ ማስታወቂያ ለተጠቃሚዎች በመልቀቅ አይደለም።
ሟቹ የአፕል መሥራች ስቲቭ ጆብስ፤ ሰዎች መረጃቸው መወሰዱ ባያስገርማቸው እንኳ እንዴት እንደተወሰደ ሊያውቁት ይገባል የሚል አቋም ነበረው።
በቅርቡ ደግሞ የወቅቱ የአፕል ዋና ሥራ አስኪያጅ ቲም ኩክ ኩባንያዎች 'ኩባንያዎች መረጃ መዝብረው ሊበልፅጉ አይገባም' ሲሉ ፌስቡክን በነገር ሸንቆጥ አድርገው ነበር።
ሳፋሪ ማለት አይፎን ላይ ወደ በይነ መረብ የሚያስገባ መስኮት ማለት ነው። ሰዎች ሳፋሪን ሲጠቀሙ መረጃቸው በፍፁም እንዳይበረበር አድርጓል አፕል።
ይህም ፌስቡክን ካበሳጩ የአፕል ድርጊቶች አንዱ ነው።
ፌስቡክ ይህ የአፕል ድርጊት ጥቃቅንና አነስተኛ 'ቢዝነሶችን' የሚገድል እንዲሁም 'ተጠቃሚዎች የተሻለ ነገር እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው' ሲል ይሞግታል።
ፌስቡክ ይህን መልዕክቱን ለሰዎች ለማድረስ ባለፈው ታህሣሥ በጋዜጣ ሁሉ ዜና አስነብቧል።
ነገር ግን አፕል ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ነው።
ታድያ የሁለቱ ግዙፍ ኩባንያዎች እሰጥ አገባ ምን ይገደኛል? ሊሉ ይችላሉ።
የአይፎን ተጠቃሚ ሆኑም አልሆኑም መረጃዎ ለሌሎች ኩባንያዎች ተላልፎ እየተሰጠ መሆኑን መርሳት የለብዎትም ይላሉ የቴክኖሎጂ ሰዎች።
ይህ መረጃዎ መንግሥታትን ጨምሮ ለማንም ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል።
ፌስቡክና ቲክ ቶክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቁሳቁስና አገልግሎት አቅራቢዎች በመሸጥ ነው ትርፍ የሚያገኙት።
የዘርፉ ሰዎች እንደሚሉት አፕል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።
ታድያ ፌስቡክ በምን ዓይነት አዲስ መላ ብቅ ይል ይሆን?












