የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ መሪዋ የተገደለባት ቻድ ወታደራዊ አመራር እንዲያበቃ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ በአማፂያን መሪዋ የተገደለባት ቻድ ወታደራዊ አመራር እንዲያበቃ ጥሪ አድርጓል።
የፕሬዚዳንት ኢድሪስን ዴቢ ግድያን ተከትሎ ሰራዊቱ ልጃቸው ለ18 ወራት ያህል ወታደራዊውን ጉባኤ ይመራል በማለት አውጀዋል።
ይህም ማለት ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ማለት ነው።
የቻድ የቀድሞ ቅኝ ገዥና በቻድ ትልቅ የጦር ሰፈር ያላት ፈረንሳይ በበኩሏ ይህንን አይነት የስልጣን ሽግግር አገሪቷ እንድትረጋጋ ሲባል በተለዬ ሁኔታ እንደምታዬውና ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው "ስርወ-መንግሥታዊ መፈንቅለ መንግሥት" ነው ሲሉ አውግዘውታል።
የንግድ ማህበራት አድማን የጠሩ ሲሆን አማፂው ቡድን ፋክት በበኩሉ ቻድ "ንጉሳዊ አገዛዝን የምትከተል አይደለችም" ሲል ተቃውሞታል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ወታደራዊ አገዛዙ ስልጣን የነጠቀበት መንገድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብኛል ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ፖርላማው የተበተነ ሲሆን የ37 አመቱ ጄኔራል ማሃማት ዴቢ ኢትኖም በመሪነት ቦታ ተቀምጠዋል።
የምክር ቤቱ 15 አባላት በያዝነው ሃሙስ ተሰብስበው በጉዳዩ ላይ የተወያዩ ሲሆን የኢድሪስ ዴቢ ስርዓተ ቀብር አርብ ከተፈጸመ በኋላ ነው መግለጫ ያወጡት።
መግለጫው በግልፅ እንዳሰፈረው በቻድ ሲቪል አስተዳደር በፍጥነት ሊመለስ እንደሚገባ አሳስቧል።
በአገሪቱ ህገ መንግሥት መሰረት ፕሬዚዳንት በሚሞትበት ጊዜ የፓርላማው አፈ ጉባኤ ስልጣኑን ተረክቦ የመጪው ምርጫ መታቀድ አለበት።
በቅርቡ በሰሜኑ ክፍል ካኔም ሪቤል ፋክት ከተሰኘው አማፂ ቡድን ጋር በነበረ ግጭት ክፉኛ ተጎድተው ህይወታቸው ያለፈው የ68 አመቱ ኢድሪስ ዴቢ ለስድስተኛ ጊዜ ተመርጠው አገሪቷን እየመሩ ነበር።
በምዕራብ አፍሪካ ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉ የጂሃዲስቶችን ቡደን በመታገል ለፈረንሳይ ቀኝ እጅ ነበሩ ፕሬዚዳንቱ። ማረፋቸው ከተሰማም በኋላ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች ሃዘናቸውን ገልፀዋል።












