የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በግድቡ ዙሪያ የአፍሪካ መሪዎችን እያነጋገሩ ነው

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪ እና የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ። ናይሮቢ ኬንያ ሚያዝያ 11

የፎቶው ባለመብት, @StateHouseKenya

የምስሉ መግለጫ, የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪ እና የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ። ናይሮቢ ኬንያ ሚያዝያ 11

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን እየተዘዋወሩ እያነጋገሩ ይገኛሉ።

ሳሚህ ሽኩሪ ኢትዮጵያ እየገነባች ካለችው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የግብጽ አቋምን ለማሳወቅ እና የፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲን መልዕክት ለማድረስ በስድስት የአፍሪካ አገራት ጉብኝት እያደረጉ ነው።

ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እስከ አሁን ወደ ኬንያ፣ ኮሞሮስ እና ደቡብ አፍሪካ የተጓዙ ሲሆን በቀጣይ የሴኔጋል፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ እና የቱኒዚያ መሪዎችን አግኝተው ያነጋግራሉ።

ሳሚህ ሽኩሪ በቅድሚያ ጉዟቸውን ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ወደሆነችው ኬንያ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በኬንያ ቆይታቸው ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የፕሬዝደንት አል-ሲሲን መልዕክትም ለፕሬዝደንቱ አድርሰዋል።

የኡሁሩ ኬንያታ ቤተ-መንግሥት፤ ፕሬዝደንቱ ከግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎቶች ላይ በተለይ ደግሞ የጋራ የተፈጥሮ ሃብት ለሁሉም የአህጉሪቱ አገራት የጋራ ጥቅም ላይ ተወያይተዋል ብሏል።

የግብጹ ልዩ መልዕከተኛ፤ ኬንያ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗን አስታውሰው በአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መካከል አለመግባባቶችን የመፍታት አቅም እንዳላት ግብጽ ታምናለች ስለማለታቸው የፕሬዝደንት ኡሁሩ ቤተ-መንግሥት በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪ እና የኮሞሮስ ፕሬዝደንት አዛሊ ኡሱማኒ።

የፎቶው ባለመብት, @MfaEgypt

የምስሉ መግለጫ, የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪ እና የኮሞሮስ ፕሬዝደንት አዛሊ ኡሱማኒ።

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከኬንያ ቆይታቸው በኋላ ቀጣይ መዳረሻቸውን ያደረጉት ወደ ኮሞሮስ መሆኑን የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አህመድ ሃፌዝ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ለኮሞሮስ ፕሬዝደንት አዛሊ አሱማኒ ከአል-ሲሲ የተላከውን መልዕክት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

የሳሚህ ሽኩሪ ሶስተኛ መዳረሻ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ነች። የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር መገናኘታቸውን ቃል አቀባዩ አህመድ ሃፌዝ አስታውቀዋል።

ሳሚህ ሽኩሪ ከፕሬዝደንት ራማፎሳ ጋር በነበራቸው ቆይታ የግድቡ ድርድር ያለበትን ሁኔታ እና የግብጽን አቋም መግለጻቸው ተጠቁሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ጋር በተያያዘ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ደብዳቤ ጽፋለች።

የኢትዮጵያ ደብዳቤ፤ የጸጥታው ምክር ቤት ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን በመለከተ ወደ ሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲመለሱ እና የአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነትን እንዲያከብሩ ጫና እንዲያሳድሩ የሚጠይቅ ነው።

ለወቅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝደንት በተጻፈው ደብዳቤ፤ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን፤ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራው ድርድር ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ የጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍን አግኝቶ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ግብጽ እና ሱዳን በመልካም መርህ ላይ ተመሠርተው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተደራደሩ አይደለም ብለዋል።

ጉዳዩን "ዓለም አቀፋዊ" ገጽታን በመስጠት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩም ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንሰትሩ በደብዳቤያቸው ማጠቃለያ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር እና በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን ድርድር ወደ ጎን ማድረግ፤ በሦስቱ አገራት መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል ብለዋል።