ቻይና የጃክ ማ ድርጅት መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያደርግ አስገደደች

ጃክ ማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና በአገሪቱ ያለውን የገበያ ስርአት ለመቆጣጠር ይረዳኛል በማለት በጀመረችው ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ተቋማትን ማሻሻል ተግባር መሰረት በቢሊየነሩ ጃክ ማ የተመሰረተው አንት ግሩፕ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲኖር አስገድዳለች።

በዚህም መሰረት አንት ግሩፕ እንደ ባንክ አይነት መዋቅር ይኖረዋል ተብሏል።

ባሳለፍነው ሕዳር ወር ላይ 37 ቢሊዮን የሚሆነው የአንት ግሩፕ አክሲዮን ሽያጭ ለገበያ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም የቻይና ተቆጣጣሪዎች ግን የድርጅቱ እንቅስቃሴ አላስተማመነንም በማለት አግደውታል።

ቻይና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ሲሆን በአንት ግሩፕ ላይ በግድ የተደረገውም ማሻሻያ የዚሁ አካል ነው ተብሏል።

የአንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው አሊባባም ቢሆን ባሳለፍነው አርብ ገበያውን ያለአግባብ በመቆጣጠር በሚል 2.8 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል መወሰኑ የሚታወስ ነው።

በአንት ግሩፕ ላይ መዋቅራዊ ለውጡን ያዘዘው የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ሲሆን ከዚህ በኋላ ድርጅቱ ጠበቅ ያለ ቁጥጥርና ክትትል ይደረግበታል።

አንት ግሩፕ በቻይና ትልቁ የክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ ስርአት ሲሆን ከ730 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች በየወሩ 'አሊፔይ' የተሰኘውን ስርአት በመጠቀም ገንዘብ ያዘዋውራሉ።

ይህ የቻይና መንግስት እርምጃ አሊባባን እና አንት ግሩፕን በጥምረት የመሰረተው ጃክ ማ ላይ የተነጣጠረ እንደሆነ እየተገለጸ ነው።

የቻይና መንግሥት ተቆጣጣሪዎች በጃክ ማ ላይ ክትትል ማድረግ የጀመሩት ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ተቆጣጣሪዎች በአገሪቱ ስራ ፈጠራን እየተፈታተኑ ነው በሚል መውቀሱን ተከትሎ ነው።

ቢሊየነሩ ይህንን ንግግር ካደረገ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቻይና መንግስት ተቆጣጣሪዎች የአንት ግሩፕ የአክሲዮን ሽያጭን አስቁመዋል።

በተጨማሪም በቻይና ትልቁ የሆነው የበይነ መረብ መገያያ አሊባባ ላይም አንዳንድ ጥሰቶችን ፈጽሟል በማለት የገበያ ሁኔታን የሚቆጣጠረው የመንግስት አካል ምርመራ ጀምሯል።

አርብ ዕለት አሊባባ 2 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል መወሰኑን ተከትሎ የድርጅቱ የአክሲዮን ገበያ 8 በመቶ አድጓል። ይህ የሆነውም ድርጅቱ አንድ ጊዜ ከተቀጣ ከዚህ በኋል መንግስት ክትትል አያደርግበትም በሚል እሳቤ ነው።