ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤርትራ ከ30 በላይ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ሰዎችን ለቀቀች
የኤርትራ መንግሥት 36 በእምነታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ ሰዎችን በዋስ መፍታቱ ተገለጸ።
ከተለቀቁት መካከል 14 ላለፉት 4 ዓመታት በዳህላክ ደሴት ታስረው የነበሩ መሆናቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
22 ደግሞ የታሰሩት ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ሲሆን አሁን የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው እንዲወጡ ተደርጓል።
ሁሉም እስረኞች ወንጌላውያን እና የጴንጤቆስጤ ቤተ እምነት አባላት መሆናቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ መረዳት ችሏል።
እእኤ በ2002 ኤርትራ ከኦርቶዶክስ፣ ከካቶሊክ እና ከሉትራን አብያተ ክርስቲያኖች ውጪ የተቀሩትን ቤተ እምነቶች የሚከለክል ሕግ አውጥታለች።
በቅርቡ የኤርትራ መንግሥት በእምነታቸው ምከንያት ታስረው የነበሩ ግለሰቦችን መልቀቁ ይታወሳል።
በመስከረም ወር ለዓመታት ታስረው የነበሩ 20 ግለሰቦች የተለቀቁ ሲሆን፣ በኅዳር ወር ደግሞ ለረዥም ዓመታት በእስር የቆዩ 28 የጆሃቫ ምስክር ተከታዮች ተለቅቀዋል።
ይኹን እንጂ የእምነት ነጻነት ላይ እንደሚከራከሩ ቡድኖች ከሆነ አሁንም በርካታ ክርስትያኖች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ እየታሰሩ ናቸው።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ የጴንጤቆስጤ እና ወንጌላውያን አማኞችን የውጭ መንግሥት መጠቀሚያ ናቸው ሲል ይከስሳል።
ኤርትራ በተለያዩ ሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በእምነት ተቋማት ላይና በተከታዮቻቸው ላይ ጭቆናና እስርን በመፈጸም በተደጋጋሚ ስትከሰስ ቆይታለች።