ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ፡ ፕሬዝደንቱ የማዕከላዊ ባንክ ገዢውን ካባረሩ በኋላ የሃገሪቱ ገንዘብ 14 በመቶ ላሸቀ
የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን የሃገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ አስተዳደሪ ማበረራቸውን ተከትሎ የቱርክ መገበያየ ሊራ 14 በመቶ ላሸቀ።
የቀድሞ የባንክ ገዢ ናሲ አግባል፤ ሊራ በጣም ዘቅጦ ከነበረበት ከፍ አድርገው ለዚህ ያበቁ ሰው ናቸው የሚል ሙገሳ ይቸራቸዋል።
ነገር ግን ፕሬዝደንት ኤርዶዋን ሳይታሰብ ባለፈው ቅዳሜ ሰውዬውን አንስተው በሌላ ተክተዋቸዋል።
ቱርክ የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪ ስታባርር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ ሶስተኛው ነው።
ባለፈው ኅዳር የተሾሙት አግባል ከ15 በመቶ በላይ እየሆነ የመጣውን የዋጋ ንረት ለማቀዛቀዝ የወለድ መጠንን ከፍ አድርገው ነበር።
የሰውዬው መባረር የሃገር ቤትና የውጭ ኢንቨስተሮችን አስደንግጧል።
አግባል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በወሰዷቸው እርምጃዎች በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እንዲቸራቸው አድርጓቸው ነበር።
ሊራ አንድ ወቅት ላይ በፈረንጆቹ 2021 አዳጊው የመገበያያ ገንዘብ ተብሎ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር ያለውን ዝቅጠት በአምስት አሻሽሎ ነበር።
ባለፈው ሳምንት ሰውዬው የወለድ መጠን 2 በመቶ እንዲጨምር ማድረጋቸውን ተከትሎ የቱርክ ሊራ ወደላይ ተመንድጎ ነበር።
በሃገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሃብቶች ቱርክ ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ እንድትቀርፅ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
አሁን ፕሬዝደንት ኤርዶዋን የማዕከላዊ ባንኩን አስተዳደር በሌላ ለመተካት በማሰባቸው ምክንያት የሊራ ዋጋ እንዳሽቆለቆለ ሊቀር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
አዲሱ የማዕከላዊ ባንኩ ኃላፊ የባንኪንግ ፕሮፌሰር ናቸው። አልፎም የገዢው ፓርቲ የቀድሞ ሕግ አውጭ ነበሩ።
ሰውዬው ከተባረሩት ኃላፊ በተቃራኒ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ወለድ መጨመር አስፈላጊ ነው ብለው አያምኑም።
የቱርክ የወለድ መጠን 19 በመቶ ደርሷል። ይህም የውጭ ሃገር ኢንቨስተሮች ገንዘባቸው በሃገሪቱ እንዲያከማቹ አድርጓቸዋል።