"ህወሓት ጦርነት እንደሚጀምር አውቀን ስንዘጋጅ ነበር" አቶ አገኘሁ ተሻገር

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር ከህወሓት በኩል ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል በማሰብ ክልሉ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ይህንን ያሉት ለአማራ ክልል ምክር ቤት የመስተዳደሩን የስድስት ወራት የሥራ ክንውን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ነው።
አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት "ጦርነቱን ህወሓት መቼ እንደሚጀምረው ባናውቅም ወደማንፈልገው ጦርነት ሊያስገባን እንደሚችል በመገንዘብ ስንዘጋጅ ቆይተናል" ብለዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግ "የክልሉ መንግሥት የይሆናል ዕቅድ አዘጋጅቶ ራስን ለመከላከል ስንዘጋጅ ስለቆየን ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት መከላከል ችለናል" በማለት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
ምንም እንኳን ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል ተዘጋጅተው እንደነበር ገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ ጦርነቱ ጥቅምት መጨረሻ ላይ ይሆናል ተብሎ እንዳልተጠበቀ ተናግረዋል።
አክለውም ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር በኩል ወረራ መፈጸሙን ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።
በተለይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ቅራቅር እና ሶሮቃ በኩል የአገር መከላከያ ሠራዊት ለዘመቻው የሚያስፈልጉትን የተለያዩ አቅርቦቶችን እስኪያጓጉዝ ድረስ የክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃቱን መመከት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
አቶ አገኘሁ ትኩረት ሰጥተው ከተናገሩባቸው ጉዳዮች መካከል ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የአማራ ብሔር አባላት ደኅንነት ጉዳይ አንዱ ነው።
ርዕሰ መስተዳደሩ በተለይም በኦሮሚያ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልሎች ውስጥ "የአማራ ተወላጆች ጥቃት የሚደርስባቸው ህወሓት በሠራው የረጅም ጊዜ ሸፍጥ ነው። ይህም ምንም ጥናት የማያስፈልገው ነባራዊ እውነታ ነው" በማለት "በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አማራ በማንነቱ ለሚደርስበት መፈናቀልና ግድያ" ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።
ከዚህ ባሻገርም የአማራ ክልል ከሚዋሰናቸው ክልሎች ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም መስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በተያያዘ በርካታ የክልሉ ተወላጆች የሚደርስባቸውን ጥቃት በቋሚነት ለመከላከል ሁለቱ ክልሎች በጋራ የሚሰሩበት ቻርተር ተሰናድቶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበት የአማራ ክልል አካባቢን በተመለከተም ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ማብራሪያ በጥቅምት ወር በትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በምዕራብ ጎንደር አካባቢዎች የሱዳን መንግሥት ወረራ መፈጸሙን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በሱዳን ኃይል የተወረሩት አካባቢዎች አሁንም በሱዳን ቁጥጥር መሆናቸውን አቶ አገኘሁ የተናገሩ ሲሆን፤ በእዚህም ሰፊ የእርሻ ቦታዎችና ካምፖች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
"ይህ ሲሆን ብዙ ጥፋት ደርሷል" ያሉት አቶ አገኘሁ፣ "በቀጣይም የበለጠ ጥፋት ሊደርስ እንደሚችል አመላካች ነገሮች በመኖራቸው የፌደራል መንግሥት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀናል" ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር የክልሉን መስተዳደር የግማሽ ዓመት የሥራ ክንውንን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ የሥራ እድልን በመፍጠር፣ ኢንተርፕራይዞችን ማሳደግ፣ ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ፣ አዳዲስ እና ነባር የመስኖ ሥራዎችን በመጠገንና በመገንባት የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎችንና ሌሎች ተግባራት አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።














