ዩኬ ለየመን የምትሰጠውን እርዳታ መቀነሷን የረድኤት ድርጅቶች አወገዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የረድዔት ድርጅቶች የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በየመን ላይ ያደረገውን የእርዳታ ቅነሳ አወገዙ።
በመቶ የሚቆጠሩ የረድዔት ድርጅቶች ተቀባይነት የለውም በሚልም ነው ያወገዙት።
በዘንድሮው ዓመት ለመካከለኛ ምስራቋ አገር፣ የመን 87 ሚሊዮን ፓውንድ እርዳታ እንደሚሰጥ እንግሊዝ ቃል ገብታለች። ከአመት በፊት የነበረው ዕጥፍ ፣ 164 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ በበኩላቸው መንግሥታቸው የየመንን ህዝብ ለመርዳት የገባውን ቃል አያጥፍም ብለዋል።
ነገር ግን የመን ከመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ አገራት መካከል የዩኬ እርዳታ ሊያሽቆለቁልባት ይችላል ከተባሉት ዋነኛዋ እንደሆነች ሾልኮ የወጣ ኢ-ሜይል አስታውቋል።
በመጀመሪያ ጉዳዩን ሪፖርት ያደረገው ኦፕን ዲሞክራሲ እንዳስታወቀው በባለፈው ወር ከመንግሥት ባለስልጣናት ሾልኮ የወጣ መረጃን መሰረት አድርጌያለሁ በማለት በሶሪያ 67 በመቶና በሊባኖስ 88 በመቶ እርዳታ ይቀንሳል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በናይጄሪያ 58 በመቶ፣ በሶማሊያ 60 በመቶ፣ በደቡብ ሱዳን 59 በመቶና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 60 በመቶ እርዳታ እንደሚቀንስ አስነብቧል።
እነዚህ የረድዔት ድርጅቶች ለመሪው ቦሪስ ጆንሰን በፃፉት ደብዳቤ ህዝቡ በድህነት፣ በበሽታና በጦርነት የተጠቁ አገራትን ፊቱን ገሸሽ ያደርጋል ብሎ መንግሥት ማሰቡ ስህተት ነው ብለዋል።
"የዩኬ መንግሥት በዚህ ወቅት የየመንን ህዝብ ችላ ብሎ የማይረዳ ከሆነ ታሪክ በጥሩ መልኩ አይዳኘውም። ከዚህ በተጨማሪ ለተቸገሩ አገራት አለሁ በማለት የምትረዳውን የዩናይትድ ኪንግደም አለም አቀፍ ስም የሚያጠለሽ ነው" ይላል ደብዳቤው
ኦክስፋም፣ ክርስቲያን ኤይድ፣ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ኬር ኢንተርናሽናልን ጨምሮ 101 ድርጅቶች ናቸው ተቃውሟቸውን ያስገቡት።
የእንግሊዙ ኦክስፋም ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳኒ ስሪስካንዳራጅ እንዳሉት "ምጣኔ ኃብታችን ተጎድቷል በሚል የሚደረግና የበርካታ ሚሊዮናውያንን የመኖችን ህይወት የሚነጥቅ የእርዳታ ቅነሳ ሃሰተኛ ኢኮኖሚ ነው። በርካቶች ቤተሰቦቻቸውን መመገብ አልቻሉም፤ ቤታቸውን አጥተዋል፤ በኮሮናቫይረስና በግጭት ምክንያትም ህይወታቸው አደጋ ላይ ነው" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ እንዲህ በጦርነት በምትበጠበጥ አገር ላይ የጦር መሳሪያ በመሸጥ "'ኢ-ሞራላዊ' ተግባር እንዲታቀብ አስጠንቅቀዋል።












