የኮቪድ-19 ክትባት ወደ ኢትዮጵያ በነገው ዕለት እንደሚገባ ተገለፀ

የኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚውለው የመጀመሪያ ዙር ክትባት በነገው እለት፣ 28/6/2013 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ክትባቱ ኮቫክስ ከተሰኘው አለም አቀፍ ጥምረት የተገኘ ሲሆን መጠኑም 2.2 ሚሊዮን ዶዝ እንደሆነም ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ክትባቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የጤና ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመለየት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለክትባቱ በዋናነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜጎች ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረት የጤና ባለሙያዎች፣ የማህበራዊ ጤና ሰራተኞች፣ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ያሉ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ሀይልም የተሳለጠ የክትባት አሰጣጥና ቁጥጥር እንዲኖር ያደርጋል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ከተለያዩ ተቋማት የተዋቀረው ሃገራዊ የኮቪድ-19 ክትባት የበላይ አስተባባሪ ኮሚቴ ክትባቱን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና ለማሰራጨት እየተደረገ ያለውን አጠቃላይ ዝግጅት በተመለከተ በትናንትናው ዕለት፣ የካቲት 26፣ 2013 ዓ.ም ውይይት ተደርጓል።

በዚህ ውይይት ላይም በዋነኝነት የኮቪድ-19 ክትባት አቅርቦትና ስርጭት አስመልክቶ በታቀደው መሰረት የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትና ዝግጅቱን መገምገሙንም ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዪት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከዚህም በተጨማሪ ክትባቱ ጥራቱን በተጠበቀ መልኩ የሚደርስበትን፣ በተቆጣጣሪ አካል እየተከወኑ ስላሉ ስራዎች፣ ክትባቱን የሚከተቡትን የተለዩ አካላትም አስመልክቶና በህዝቡ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ ውይይቶች ተደርገዋል።

በተጨማሪም አገሪቷ ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር በተያያዘ ልታከናውናቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተም የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አቅጣጫ መስጠታቸውም ተገልጿል።

በውይይት መድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አጄንሲና የተለያዩ የልማት አጋር ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ኮቫክስ ምንድነው?

የኮሮናቫይረስ ክትባት ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ ሃብታም የሚባሉቱ አገራት ናቸው ክትባቱን በገፍ እየገዙ ዜጎቻቸውን እየከተቡ ያሉት።

በዶክተር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት አማካይነት የተዘረጋው ኮቫክስ የተሰኘው ማዕቀፍ ደሃ አገራት ክትባቱን ለማግኘት ብዙ እንዳይጠብቁ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል።

ኮቫክስ (COVAX) ምጣኔ ኀብታቸው ደካማና መካከለኛ ለሆኑ አገራት ክትባቱን ለማቅረብ ያለመ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የተመሰረተ ኢኒሼቲቭ ነው።

ሁሉም የአፍሪካ አገራት ይህንን ኢኒሼቲቭ ተቀብለውታል።

በዚህ ማዕቀፍ መሠረት ሃብታሞቹ አገራት አቅም የሌላቸውን አገራት በገንዘብ እንዲያግዙ ይደረጋሉ።

በአንድ ዓመት ብቻ በ190 አገራት ሁለት ቢሊዮን ክትባቶችን ለማሠራጨት ታልሟል።

በተለይ ደግሞ 92 ደሃ የሚባሉ አገራት ከሌሎች 98 አቅም ካላቸው አገራት እኩል ክትባቱን እንዲቀበሉ ይደረጋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናቸው።

ይህም ማለት አፍሪካ በዚህ ኢኒሼቲቭ በኩል፣ 220 ሚሊዮን ክትባቶችን ታገኛለች።

ነገር ግን እንደ ሴኔጋል ያሉ ጥቂት አገራት ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ ክትባት ማግኘት ችለዋል።

ፕሮግራሙ እስካሁን ድረስ ለክትባት የሚሆን 6 በሊየን ዶላር ማሳበሳብ ችሏል። ቢሆንም ተጨማሪ 2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል እየተባለ ነው።

ምንም እንኳ ፕሮግራሙ ቀርፋፋ ነው እየተባለ ቢተችም የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ አሁን ጋና የደረሰው ክትባት የመጀመሪያው ዙር ነው ብለዋል።

እኤአ በ2021 መጨረሻ ላይ ኮቫክስ 2 ቢሊዮን የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመግዛት እቅድ ይዟል።

አፍሪካ ለአህጉሩ የሚሰራጭ ለጊዜው 270 ሚሊዮን 'ዶዝ' (መጠን) የኮቪድ-19 ክትባት በአፍሪካ ሕብረት በኩል ማግኘቷ ተገልጿል።

አጠቃላይ የተገኘው ክትባት በዚህ ዓመት ጥቅም ላይ እንደሚውል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ቃል ገብተው ነበር።

ይህ ክትባት ከዚህ ቀደም ቃል ከተገባው 600 ሚሊየን 'ዶዝ 'ተጨማሪ ቢሆንም አሁንም ግን ሙሉ አህጉሩን ለመከተብ በቂ አይደለም።

በዚህም የዓለማችን ድሃ አገራት ከሃብታም አገራት ይልቅ ክትባቱን ለመከተብ ረዥም ጊዜ ሊጠብቁ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ከኮቫክስ የክትባት ትብብር ተቋም ጋር በመሆን እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝባቸውን ለመከተብ እየሰሩ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ምንም እንኳን በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ዝቅተኛ ቢሆንም በአንዳንድ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በድጋሜ እየጨመረ ነው።

በኢትዮጵያም ወረርሽኙ ከተከሰተባት እለት ጀምሮ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሬ እያሳየ ሲሆን እስካሁንም ባለው 164 ሺህ 73 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ከነዚህም ውስጥ 137 ሺህ 431 ሲያገግሙ 2 ሺህ 404 ሞተዋል።