ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿን ያጠቃው የአንበጣ መንጋ በምን ሁኔታ ላይ ነው?

አንበጣ የያዘች ኢትዮጵያዊት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ከወራት በፊት የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ክፍሎች ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት ይህንን መንጋ ለመዋጋት በባሕላዊና ዘመናዊ መንገድ ለመከላከከል ጥረት አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ።

ነገር ግን ይህ ሰብል አውዳሚ የአንበጣ መንጋ ጠፍቶ ይሆን?

ከሰሞኑ የዓለም ምግብ ድርጅት [ፋኦ] ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው የአንበጣ መንጋው አሁንም በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ለምሳሌ ሶማሊያ ውስጥ አዳዲስ የአንበጣ ዕጮች እየተፈለፈሉ እንደሆነ ነው ፋኦ የሚጠቁመው።

አዳዲሶቹ መንጋዎች ከሰሜን ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል [ፑንትላንድ] እየመጡ እንዳለ የድርጅቱ ዘገባ ይጠቁማል።

በሰሜን ምስራቅ የምትገኘው ሶማሊላንድም የዚህ አንበጣ መንጋ ሰለባ ልትሆን እንደምትችል ተጠቁሟል።

ከእነዚህ አካባቢዎች የሚነሳው የአንበጣ መንጋ ወደ ሰሜናዊ ክፍል በማምራት ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል እየተስፋፋ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ እድገታቸውን ያልጨረሱ አንበጣዎች በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲ፣ ባሌና ቦረና ይገኛሉ።

መሰል የአንበጣ መንጋዎች በደቡብ ክልል በኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አማሮና ደራሼ እየተስፋፉ ይገኛሉ።

ወደ ኬንያ ስንመጣ ምንም እንኳ ከኢትዮጵያና ሶማሊያ የሚፈልሱ የአንበጣ መንጋዎች ቢቀንሱም በሰሜናዊና ማዕከላዊ የሃገሪቱ ክፍሎች አዳዲስ ዕጮች እየተፈለፈሉ ነው።

ኬንያ ከሌሎች ሃገራት በተለየ ባለፉት ጥቂት ቀናት የአንበጣ መንጋዎች መቀነስ እየተመዘገበባት ነው።

በኬንያና በኢትዮጵያ የተጠናከረ የሰማይና የምድር ላይ አንበጣ የማጥፋት ሥራ መከናወኑ እየቀነሰ ላለው ቁጥር አስተዋፅዖ አድርጓል ይላል የዓለም ምግብ ድርጅት።

ከዚህ በተጨማሪ ለአንበጣ መንጋ መፈልፈልና መስፋፋት ጉልህ ሚና ያለው ዝናብ አለመኖር በጎ ዜና ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህ ምክንያት ከመጋቢት እስከ ሰኔ ድረስ ያለው ለአንበጣ መንጋ አመቺ የሆነው ጊዜ እምብዛም መንጋው የሚስፋፋበት ላይሆን ይችላል ተብሏል።

በሌላኛዋ ጎረቤት ሃገር ሱዳን በቀይ ባሕር በኩል ከኤርትራ አካባቢዎች የሚመጡ ጥቂት የአንበጣ መንጋዎች አሁን እንደሚስተዋሉ የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል።

ሳዑዲ አረቢያና የመንም ከሌላው ጊዜ በተለየ የአንበጣ መንጋ ቁጥር እየቀነሰባቸው የመጡ ሃገራት ናቸው።

በበረሃ አንበጣ ወረራ በአህጉሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችውን ኢትዮጵያና የአካባቢው ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ማዕከል በሆነችው ኬንያ እንዲሁም ለአስርታት አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው ሶማሊያ ክፉኛ የተጠቁ አገራት ናቸው።

የአንበጣ መንጋው የጤፍ ምርትን ጨምሮ ሽንኩርትን የመሳሰሉ የአትክልት ምርቶችን ሳይቀር ማውደሙ ይታወሳል።

ካርታ