የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስ ከቤተ-ሙከራ የማምለጡ እድል እጅግ የተመናመነ ነው አለ

የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያደረገች ሴት በዉሃን ከተማ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የኮሮናቫይረስ መነሻን ለማወቅ ወደ ቻይና ዉሃን የተጓዘው ዓለም አቀፍ የአጥኚዎች ቡድን ‘ኮሮናቫይረስ ከቻይናው ላብራቶሪ አምልጧል’ የሚላውን መላምት ውድቅ አደረጉ።

የዓለም ጤና ድርጀት አጥኚ ቡድንን የሚመሩት ፒተር ኢምባርክ፤ ቫይረሱ ከዉሃን ቤተ-ሙከራ አምልጧል የሚለው መላምት ትክክለኛ የመሆኑ እድል በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል። የአጥኚ ቡድኑ መሪ የቫይረሱን ትክክለኛ ምንጭ ለማወቅ ተጨማሪ ምርምሮች መካሄድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ይህ የአጥኚው ቡድን አስተያየት የተሰጠው፤ የቫይረሱን መነሾ ለማወቅ ወደ ቻይና የተጓዘው ቡድን የቻይና ተልዕኮውን በጨረሰበት ወቅት ነው። በቻይናዋ ሁቤ ግዛት በምትገኘው ዉሃን ከተማ ነበር ኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበው።

እስካሁን ቫይረሱ ከ106 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያጠቃ ሲሆን ከበሽታው ጋር በተያያዘ የ2.3 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት አልፏል። የአጥኚ ቡድኑ መሪ ፖተር ኢምባርክ፤ በዉሃን ያደረጉት የምርምር ሥራ አዳዲስ መረጃዎችን ያስገኘላቸው ቢሆንም የወረርሽኙን ገጽታ የሚቀይር ይህ ነው የሚባል አዲስ መረጃ አለመገኘቱን ተናግረዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ኮሮናቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው ልጆች እንደተላለፈ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይሁን እንጂ ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዴት እንደሚተላለፍ በትክክል ማረጋገጥ አልቻሉም።

ባለሙያው ጨምረው እንደተናገሩት ቫይረሱ ታኅሣሥ 2012 ለመጀመሪያ ጊዜ በዉሃን ሪፖርት ከመደረጉ በፊት በሌሎች የቻይና ግዛቶች ተሰራጭቶ እንደነበር ምንም ማረጋገጫ የለም ብለዋል።

የቻይና የጤና ኮሚሽን ባልደረባ የሆኑት ሊአንግ ዋኒአን ኮሮናቫይረስ በዉሃን ከመታየቱ በፊት በሌሎች አከባቢዎች ሳይሰራጭ አይቀርም ብለው ነበር። የዓለም ጤና ድርጅት አጥኚ ቡድን የቫይረሱን መነሾ ለማወቅ ወደ ቻይና ሲያቀና የቻይና መንግሥት በጉዳዩ ደስተኛ አልነበረም።

ወራትን ከፈጀ ድርድር በኋላ ነበር ቤጂንግ አጥኚ ቡድኑን የተቀበለችው። አጥኚ ቡድኑም በቻይና በነበረው ቆይታ በቻይና መንግሥት የቅርብ ክትትል ሲደረግበት ነበር ተብሏል።